በሐረር ተቃውሞ ያሰሙ ተፈናቃይ ነዋሪዎች ግድያ ተፈጸመባቸው

 ሐረር ውስጥ ቁጥሩ ያልታወቀ ሰው መገደሉን ምንጮች ጠቆሙ፡፡ በዛሬው ዕለት የተፈጸመውን ግድያ በዋነኛነት ሲመራ የነበረው በስፍራው የሰፈረው መከላከያ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስም ቁጥሩ ሊታወቅ ያልቻለ ተፈናቃይ በጥይት ተመትቶ መሞቱን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ እንደ መረጃዎች ገለጻ፣ ከሶማሌ ክልል ተፈናቅለው በሐረር የሰፈሩ የኦሮሞ ተወላጆች በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ተቃውሞ ማሰማታቸው ለግድያው መንስኤ ሊሆን ችሏል፡፡ ተፈናቃዮቹ ‹‹እርዳታ ጭኖ ሲመጣ የነበረ መኪና ለምን ወደ ሐረር እንዳይገባ ይከለከላል›› የሚል ቅሬታ ማንሳታቸውን የገለጹት ምንጮች፣ ይህም ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር ሊያጋጫቸው እንደቻለ ምንጮቹ አክለው ገልጸዋል፡፡

ለተፈናቃዮች እርዳታ ጭኖ ሲመጣ የነበረ መኪና ወደ ሐረር እንዳይገባ መደረጉ ትልቅ ተቃውሞ ቀስቅሶ እንደነበር ታውቋል፡፡ በዚህም የተነሳ እርዳታ ሲጠብቅ የነበረው ተፈናቃይ መኪናው ለምን ወደ ሐረር እንዳይገባ ይከለከላል በሚል ምክንያት በስፍራው ከነበሩ ወታደሮች ጋር ሊጋጭ ችሏል፡፡ ይህም ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት እንደሆነ የገለጹት ምንጮች፣ በስፍራው ያለው የወታደሮች ቡድን አጋጣሚውን ተጠቅሞ ግድያ መፈጸሙን ምንጮቹ አክለው ገልጸዋል፡፡

ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ የሔደው ይኸው ግድያ ዛሬም ቀጥሎ መዋሉ ሁኔታውን በእጅጉ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡ በኦሮሚያ እና ሶማሊ ክልል የተፈጠረውን ግጭት ለማብደረድ ወደ ስፍራው ተልኳል የተባለለት መካላከያ ሰራዊት፣ መልሶ የግጭት መንስኤ መሆኑ እና ግድያ መፈጸሙ በስፍራው ያለውን ውጥረት አንድ እርከን ከፍ አድርጎታል፡፡ ይህ ዜና አስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ በሐረር በተለያዩ አካባቢዎች ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃይ ሰዎች፣ ተቃውሞ እያሰሙ ነበር፡፡ ከቅርብም ሆነ ከሩቅ የተኩስ ድምጽ ሲሰማ እንደነበር ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ምንጭ: ዘ ሀበሻ

2 responses

  1. Haha, if you want me to understand, please translate….! Best wishes, Rob

  2. Ok no problem i forward the english version soon.

Leave a comment