በጠብመንጃ አፈሙዝ እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊታፈን የተሞከረው የወጣቱ ትውልድ ጥያቄ

 

 

ላለፉት 25 ዓመታት በጠብመንጃ ሀይል እና በከፋፍለህ ግዛ ስልት ሀገሪቷን ጠርንፎ በመያዝ የገዛው ህወሀት ኢህአዴግ አሁን ላይ በሀገሪቷ ከዳር እስከዳር የተነሳውን ህዝባዊ እምቢተኝነት ተከትሎ ወደ መቃብር ሊገባ አፋፍ ላይ ይገኛል፡፡ የህዝብን ተቋውሞና ብሶት አዳምጦ ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በግድያ፣ በጅምላ እስራት እና አሰልቺ በሆነ ፖለቲካዊ የፕሮፓጋንዳ ቃላት ሽንገላዎች ለማለፍ ሲዋትት እየተስተዋለ ነው። ህወሀት ኢህአዴግ አሁንም በመላ ሀገሪቷ የተነሳውን ተቋውሞ እንደለመደው ከልማት ቱርፋቶች አለመቋደስ እና ከመልካም አስተዳደር ጉድለቶች ጋር ለማያያዝ ሲዋትር ይታያል፡፡ በአመታዊው የፓርላማ የስራ ዘመን መክፈቻ ስነስርአት ላይ በፓርላማ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግራቸውን ያደረጉት / ሙላቱ ተሾመ በሀገሪቷ በተያዘው ዓመት ለወጣቶች የስራ እድል የሚከፍቱ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ የሚውል 10 ቢሊየን ብር በላይ በጀት መመደቡን መቶ  በመቶ ብቻቸውን በተቆጣጠሩት ፓርላማ ውስጥ ለተገኙት ተሰብሳቢዎች ገልፀዋል፡፡ ይህ የፕሬዝዳንቱን ንግግር ተከትሎ የህወሀት ኢህአዴግ ማላዘን አሁንም ስርአቱ ሁሉንም ነገር በተለይም የህዝቡን የነፃነት ፍላጎት በገንዘብ ሀይል ልመልስ እችላለው በሚል እብሪት መወጠሩን ከማሳየቱም በተጨማሪ የሀገሪቷ ኢኮኖሚ በአሁኑ ሰአት ይህንን ለማድረግ የሚያስችል አቅም አለው ወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡

 

ምክንያቱም ኢኮኖሚው በራሱ ከህዝባዊው ተቋውሞ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ የወደቀ በመሆኑ ነው፡፡ ከህዝባዊው ተቋውሞ ጋር በተያያዘ ኢፍትሀዊው የፍትህ ስርአት እና ኢፍትሀዊው የሀብት ክፍፍል ያንገሸገሻቸው የሀገሪቷ ዜጎች በአገዛዙ ንብረቶች እና ከአገዛዙ ጋር በሞመዳሞድ ሀገሪቷን በመዝረፍ ሀብት ያካበቱ ግለሰቦችን ንብረቶች አውድመዋል፡፡ ይህም የሚያሳየን ነገር ቢኖር በአንድ በኩል ህወሀት ኢህአዴግ አመጣሁት በሚለው የኢኮኖሚ እድገት ብዙሀኑ ህዝብ ተጠቃሚ ባለመሆኑ የተነሳ ንብረቶቹ ላይ የባለቤትነት ስሜት ወጣቱ ትውልድ እንዳያድርበት መንስኤ ስለመሆኑ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ በጠብመንጃ አፈሙዝም ሆነ በአፋኝ እና በጠርናፊ ፓሊሲ እንኳ ቢሆን ሀገሪቷን የመምራት አቅሙ ሙሉ ለሙሉ የተሟጠጠበት ደረጃ ላይ መድረሱን ነው፡፡ ብዙሃኑን ዜጎች ያገለለ ወገንተኛነት እና መንደርተኛነት የተጠናወተው ይህ ስርአት የጥቂት ስብስቦችን ኑሮ እና ኪስ ከመሙላት ባለፈ ሰዋዊ እና ቁሳዊ ሀብትን በማስተሳሰር የብዙሀኑን ህዝብ ኑሮ ሊያሻሽል ስለአለመቻሉ ከህወሀት ኢህአዴግ ስርአት በላይ ማሳያ ያለ አይመስለኝም፡፡ ህግ አውጪ፣ ህግ ተርጓሚ እና ህግ አስፈፃሚ የፍትህ ተቋማት መሆናቸው ቀርቶ ከአንድ ፓርቲ የወጡ ግለሰቦች በሆኑበት የሀገራችን የኢኮኖሚ ስርአት በምንም ተአምር ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል ሊኖር አይችልም፡፡  በተጨማሪም የቀድሞዎቹ ታጋዮች የአሁኖቹ ሀገር አስተዳዳሪዎች ሀገር ከማስተዳደር ባለፈ በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ስርአት ላይ በነጋዴነት፣ በአምራችነት፣ በህንፃ አከራይነት በአስመጪ እና ላኪነት ተሳታፊ በሆኑበት ሁናቴ በምንም ተአምር ነው የግል ባለሀብቱ ሀብቱን እና እውቀቱን ሀገሪቷ ላይ ለማፍሰስ ተነሳሽነት ሊኖረው አይችልም፡፡

በሀገራችን ያለውን ብዙሀኑን ህዝብ በአማካይ ስናየው 65% በላይ የሚሆነው በወጣትነት እድሜ ላይ የሚገኝ ነው ፡፡ ከሀገሪቷ አጠቃላይ ህዝብ ብዙሀኑ ህዝብ በወጣትነት የእድሜ ክልል ላይ መገኘቱ  ለአንድ ሀገር ሁለት በተለያዩ ጠርዝ የተቀመጡ አዎንታዊ ጥቅሞች አሉት ፡፡ አንደኛው በወጣትነት እድሜ ላይ የሚገኝን የስራ ተነሳሽነት፣ እምቅ ጉልበት እና ብሩህ አእምሮን በመጠቀም የአንድን ሀገር ኢኮኖሚ ለማሻሻል ግብአት ማድረግ መቻሉ ሲሆን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ያለው አዎንታዊ ጥቅም ደግሞ የወጣትነት እድሜ ከሚፈልገው ነፃነት ጋር በተያያዘ ለአንባገነኖች የሀይል አገዛዝ እምቢኝ አሻፈረኝ ከሚለው ተፈጥሮአዊው የወጣትነት ባህሪ ጋር ይገናኛል፡፡ ይህም ማለት ወጣቱ ሀይል በአንድ በኩል ለሀገሪቷ ኢኮኖሚ የማእዘን ዲንጋይ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ለነፃነት መስፈን ዘብ የሚቆም ሀይል ነው እንደማለት ነው፡፡ ላለፉት ሀያ አምስት አመታት ስርአቱ የወጣቱን ትውልድ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ትውልዱ በባሰ ሁኔታ ለዘርፈ ብዙ ድህነት ተጋላጭ እንዳደረገው በወጣቱ ላይ የደረሰው እና እየደረሰ ያለው ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያ መገለሎች ማሳያ ናቸው፡፡ በወጣቱ ትውልድ ላይ ስርአቱ ካደረሰው የከፋ በደል ውስጥ በእኔ እምነት አብዛኛውን ወጣት ትውልድ ከንብረት ባለቤትነት ማሸሽ፣ በሀገሩ ሀብት እና ንብረት ውሳኔ ሰጪ እንዳይሆን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጫና ማድረግ እንዲሁም ያሰበውን እና ያመነበትን የፓለቲካ አመለካከት እንዳያራምድ ተፅእኖ እና እቀባ ማድረግ ዋነኛዎቹ ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ።

 

በእኔ እምነት በአማራ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች የሚገኙ የኢትዮጲያ የቁርጥ ቀን ወጣቶች ከአገዛዙ አፈሙዝ ጋር ተጋፍጠው ያሳዩትን እምቢተኝነት ለተመለከተ የሀገሬ ወጣት ስርአቱን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመጣል ቆርጦ መነሳቱን ያመላክታል፡፡ ሞት አይፈሬ ወጣቶች እንደ አሸን በመላ ሀገሪቷ በሞሉበት በአሁኑ ወቅት ስርአቱ የወጣቱን የነፃነት ጥያቄ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እፈታዋለው ብሎ በሀገሪቷ ለስድስት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ ማወጁን ተናገሯል፡፡ስርአቱ ለብዙሀኑ የወጣቱ ትውልድ የነፃነት ጥያቄ ለሚሰጠው የተንሸዋረረ መልስ መንስኤው በአንድ በኩል ስርአቱ እና ወጣቱ ትውልድ መሀል በአስተተሳሰብ እና በህይወት መስመር መሀል ልዩነት በመኖሩ የተነሳ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ስርአቱ ከሀገሪቷ ሰማይ ስር የሚነሱ ጥያቄዎችን በአፋኝ አዋጅ እና ከጠብመንጃ አፈሙዝ ባለፈ መመመለስ ባለመቻሉ የተነሳ ይመስለኛል፡፡ስርዓቱ 25 ዓመታት በኋላም ከአውራ ፓርቲ አስተሳሳብ ባልወጡ እና አሸናፊነትን ብቻ ማእከል ባደረጉ አመራሮቹ በበላይነት የሚዘወረው ህወሀት ኢህአዴግ አሁንም በህይወት ዘመኑ ከህወሀት ኢህአዴግ ውጪ ሌላ መንግስት አይቶ ከማውቀው አዲስ የለውጥ ሀይል ጋር ተፋጧል፡፡ ወገንተኝነት እና ዘረኝነት የነገሰበት ስርአተ ኢኮኖሚ ብዙሀኑን ህዝብ ለዘርፈ ብዙ ድህነት በማጋለጥ ጥቂቶች ብቻ የተደላደለ ህይወት እንዲኖሩ መንስኤ ይሆናል፡፡ የዚህ አይነቱ ስርአት አስከፊ ውጤት ደግሞ የቱንም ያህል ህዝቡ በኢኮኖሚያዊ ችግር ቢተበተብ የህዝብን ችግር ከመፍታት ይልቅ በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት እንዲሉ ስርአቱ ሙሉ ትኩረቱን ዘረፋ እና ስልጣንን ማስጠበቅ ላይ ማድረጉ ነው፡፡ ይህ ክስተት ደግሞ በሀገራችን አሁን ላይ እንደሚታየው አይነት ህዝባዊ ቁጣ እንዲነሳ መንስኤ ይሆናል፡፡

የሀገራችን ህዝብ በተለይም ወጣቱ ትውልድ የህወሀት ኢህአዴግ ስርአት የሌብነት ስርአት ስለመሆኑ፣ የህወሀት ኢህአዴግ ስርአት የቋሚ ሽፍቶች ስርአት ስለመሆኑ ከምስራቅ እስከ ደቡብ፣ ከደቡብ እስከ ምእራብ ላለው አሁን ላይ ነጋሪ ሳያስፈልገው የገባው ይመስለኛል፡፡ አሁን ላይ በሀገራችን ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ የሚታየው የህዝቦች ጥያቄ የህወሀት ኢሃዴግ ቋሚ ሽፍታነት ባህሪ የፈጠረው እና የወለደው ነው፡፡ የጥቂት ሽፍቶች ስብስብ የሆነው ህወሀት ኢህአዴግ ለዘረፍው ሀገራዊ ሀብት መንስኤ የሆነውን ስልጣኑን ለማስጠበቅ እና ዘለቄታዊነቱን ለማረጋገጥ ህዝቦችን ማጋጨት፣ ማፈናቀል ላለፉት 25 አመታት ዋነኛ ተግባሩ አድርጎታል፡፡በተጨማሪም ይህ ሙት ስርአት ከበፊቱ በባሰ መልኩ በአሁኑ ወቅት የህዝብን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ህዝብን መግደል ስራዬ ብሎም ተያይዞታል፡፡ የአለም ታሪክ እንደሚነግረን ህዝብን ያሸነፈ ስርአት ስለአመኖሩ ነው፡፡ በመሆኑም የህወሀት ኢህአዴግ የቋሚ ሽፍትነት እና የዘረኝነት ባህሪ አንገፍግፎት በሀገራችን ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ቁጣውን እየገለፀ ያለውን የብዙሀኑን ህዝብ ጥያቄ እና ብሶት በጠብመንጃ እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስቆም መሞከሩ በእኔ እምነት ባህርን በጭልፋ አይነቱ ሞኝነት ነው፡፡

መፍትሄው የህዝቡን በተለይም የወጣቱን ትውልድ ማህበራዊ፣ ፓለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቄዎች መመለስ ነው፡፡ የብዙሀኑን ህዝብ በተለይም ደግሞ የወጣቱን ትውልድ ጥያቄ ለመመስ ደግሞ ቋሚ ሽፍትነት እና ዘረኝነት መገለጫው ለሆነው ህወሀት ኢህአዴግ ከቶውንም አይቻለውም፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ አምርሮ እየተቃወመ ያለው የህወሀት ኢህአዴግን ቋሚ ሽፍትነት፣ የህወሀትን የበላይነት እና የህወሀት ኢህአዴግን የዘረኝነት አገዛዝ ነውና፡፡

 

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: