አንካሳው የኢትዮጵያ ኢንደስትሪያላይዜሽን : By Sebat Kilo

(ሜሮን አ. እና ዐቢይ ተክለ ማርያም)

መጋቢት 18 ቀን 1984 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ፋኩልቲ አዳራሽ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የሚሰጥ ሌክቸር ለማዳመጥ በታደሙ ተማሪዎች እና መምህራን ተጣቧል። እንዲህ ዐይነት ሌክቸር በዩኒቨርስቲው ሲሰጥ ከ18 ዓመት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው። አዳራሹ የተጨናነቀበት ምክንያት ከሌክቸሩ ታሪካዊነት ጋራ በተያያዘ ብቻ አይደለም። ሌክቸሩ የሚሰጠው በታላቁ ኢኮኖሚስት እሸቱ ጮሌ ነው።

የዶክተር እሸቱ ሕይወት በርካታ ምሑራን ባልተገራ ሕልማቸው እንኳን ሊያልሙት የሚችሉት አይደለም። የተማሪዎች ንቅናቄ ንቁ ተሳታፊ እና መሪ፣ የአርትስ ፋኩልቲ የቻንስለር የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ፣ ሁለት ትውልድ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሞያዎችን ያስተማሩ፣ መጽሐፍ በ21 ዓመታቸው የጻፉ፣ በ27 ዓመታቸው የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙ፣ ከ50 በላይ ጥናታዊ ጽሑፎችን እና መጻሕፍትን ያሳተሙ፣ በበርካታ የዓለም አቀፍ የፍትህ እንቅስቃሴዎች የተሳተፉ፣ በአይቪ ሊግ ዩኒቨርሲቲ ያስተማሩ፣ ገጣሚ እና የወጎች ጸሐፊ።

ዶክተር እሸቱ ከብዙ ኢኮኖሚክስ ምሁራን ይለያሉ። በርካታ ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ግጥሞችን እና ሥነ ጽሑፎችን እንዲሁም የፍልስፍና ሥራዎችን በማፍተልተል ነበር። በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም የማይታወቁትን ፐርሲ ሸሊ የመሳሰሉ ገጣምያን ሕትመቶችን ከተቀበሩበት ቆፍረው አውጥተው ማንበብ ይወዳሉ። በንግግሮቻቸው እና በጽሑፎቻቸው ውስጥም ከእነዚህ ሥራዎች ያገኟቸውን ውብ ቃሎች እና ሐረጎች ጣል ማድረግ ይቀናቸዋል። ይህ ከኢኮኖሚክስ ውጪ በንባብ ያካበቱት ሰፊ እውቀት በኢኮኖሚክስ ሥራዎቻቸው ላይ ተፅዕኖ አድርጓል። ለምሳሌ ዶክተር እሸቱ ልክ እንደ ታዋቂው ኢኮኖሚስት እና ፈላስፋ አልበርት ሂርሽማን ቅራኔን ያረገዙ የኢኮኖሚክስ ጥያቄዎችን ማንሳት ይወዳሉ። ለጥያቄዎቹ የሚሰጧቸው መልሶችም በተቃርኖ የታጀቡ ናቸው።

“የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጤንነት ምን ይመስላል?”

“ኢኮኖሚው ደህና ነው፤ የሕዝቡ ኑሮ አሽቆለቆለ እንጂ”

“ስለ አገሪቱ ኢንዱስትሪሊያዜሽን ምን ይላሉ?”

“ባለበት ለመርገጥ መሮጥ አለበት።”

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያላይዜን ከ30 ዓመታት በላይ የእሸቱ ጮሌን የጥናት እና ምርምር ቀልብ ወስዷል። የመጋቢት 1984 ሌክቸራቸውን ግማሽ ጊዜ የሰዉትም “የአገሪቱ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ለምን ይድኻል?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በመሞከር ነው። የኢትዮጵያ የመጀመርያው የኢንዱስትሪያል ፖሊሲ በ1947 የክረምት ወራት ከዩጎዝላቪያ በመጡ ኤክስፐርቶች ሲረቀቅ ዶክተር እሸቱ በነገሌ ቦረና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነበሩ። ፖሊሲው “የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በፍጥነት ወደ ዘመናዊነት ያሸጋግራል” ተብሎ ብዙ የተደሰኮረለት በ1950 የወጣው የመጀመርያ የዐምሥት ዓመት የልማት ፕሮግራም የጀርባ አጥንት ነበር። ዐፄ ኀይለሥላሴ እና አማካሪዎቻቸው ወደተለያዩ አገሮች- በተለይ ባለጠጎቹ ጋር እየተጓዙ “ኢትዮጵያን የሚያስፈነጥር ፖሊሲ” አለን እያሉ ያሻሽጡም ነበር። ንጉሡ ኢንዱስትሪያል ፖሊሲያቸው ልክ እንደኾነ፣ መንግሥታቸው እና የፍትሐ ብሔር ወንጀለኛ መቅጫ ሕጎቻቸው አክብደው ይመለከቱ ነበር። ለኻያ ዓመታት በብርታኒያ እና በአሜሪካ ኢክስፐርቶች በተነደፉ ጨቅላ ኢንዱስትሪያል ፖሊሲዎች አገሪቱን ሲመሩ ቆይተው አሁን በደንብ የተጠና፣ የተደራጀ እና በዋናነት በዩጎዝላቫውያን የተቀረጸ ቢኾንም በርካታ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት ፖሊሲ አግኝተዋል። ኢትዮጵያ ይህን ፖሊሲ ስታወጣ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ከኮሎኒያሊዝም አልተላቀቁም። በ1940 አኮብኩባ ምትሃታዊ የእድገት በረራ ያደረገችው ደቡብ ኮርያም እንዲህ ዐይነቱን ፖሊሲ ለመገንባት ገና “ተፍ ተፍ” እያለች ነበር። ዶክተር እሸቱ የ1984ቱን ሌክቸር ሲሰጡ ፖሊሲው የ36 ዓመት ጎልማሳ ኾኗል። በእነዚህ ዓመታት አገሪቱ የዐምሥት ዓመት የልማት ፕሮግራሞችን እንደ ርካሽ ለዋውጣለች። ኢንዱስትሪያል ፖሊሲው ኢምፖርት መተካት (import substitution) በሚል መሪ ሐሳብ ተጀምሮ ተከልሶ፣ ተለውጦ፣ ተስተካክሎ ብዙ ተጉዟል። ነገር ግን ዶክተር እሸቱ በ1967 ለመጀመርያ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያላይዜሽን በተመለከተ ባሳተሙት ጽሑፍ የጠየቁትን ጥያቄ ሳይሸርፉ ሳይሸራርፉ አሁንም እየጠየቁ ነው። “የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪሊያዜሽን ለምን ይድኻል?”

በፍጥነት ወደ 2006 እንምጣ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ለአገሪቱ ጂዲፒ ያለው ድርሻ 10 በመቶ አካባቢ ነው። ይህ ድርሻ የዐፄ ኀይለሥላሴ ሦስተኛ የአምስት ዓመት መጠናቀቂያ ወቅት ከነበረው ጋራ ተመሳሳይ ነው። ላላፉት አርባ ዓመታት እዚህ ግባ የሚባል ንቅናቄ (motion) የለም። ሊናጥ እንደ ተዘጋጀ ወተት ርግት ብሏል። እሸቱ ጮሌ በ1984 የጠየቁትን ጥያቄ አሁንም መጠየቅ ይቻላል። “የአገሪቱ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ለምን ይድኻል?” በቅርቡ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የሚደረጉ ሰሚናሮችን ብትከታተሉ “መልሱን አግኝተነዋል” የሚሉ ኢኮኖሚስቶች እና ፖሊሲ አውጪዎች አንድ ፋሽናዊ ትንተና ያቀርባሉ። ብዙዎቹ የሚናገሩት ተመሳሳይ ቋንቋ ስለኾነ “ሂፒስተር ኢኮኖሚክስ” ብየዋለሁ። “ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ለማስፋፋት ከመሞከሯ በፊት ልክ የምሥራቅ እስያ አገሮች እንዳደረጉት ቀዳሚ ትኩረቷን ማድረግ የነበረባት የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ላይ መኾን ነበረበት” ይላል ይኽ መልስ። በቀላሉ ሊበጠሱ እና ሊበሉ የሚችሉ አስጎምጂ ፍራፍሬዎችን (low hanging fruits) ትታ መሀል ላይ ያሉትን ልትሸመጥጥ ስትሞክር ወደቀች ይላል ክሱ። ትችቱ ያነጣጠረው በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይኾን በአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ላይም ነው። በተሳሳተ ስሌት ላይ የተመሠረቱ ፖሊሲዎች ጋሪውን ከፈረሱ አስቀደሙ።

ከሰር አርተር ሉዊስ ጋራ ፍልሚያ

የዚህ ሐሳብ አቀንቃኝ እና የስኀተቱ ዋነኛ ምንጭ አድርገው የሚያቀርቡት በዴቨለፕመንታል ኢኮኖሚክስ 24 – ካራት ወርቅ ጥናት ተብሎ የሚቆጠረውን የሰር አርተር ሉዊስን የዱዋል ሴክተር ሞዴል ነው። ይህን ሞዴል በሚገባ ለመረዳት ኒዮ ክላሲካል ኢኮኖሚክስ ቲዮሪ ስለ አባሮ መያዝ (catch-up) እድገት የሚለውን በመጠኑ መዳሰስ ያስፈልጋል። ኢኮኖሚስቶች እንዲህ ዐይነቱን ከኋላ ተነስቶ በፍጥነት የመሮጥ ግንኙነት (convergence) ይሉታል። የግንኙነት ቲዮሪ እንዲህ ይላል። ድኻ አገሮች ከኃብታም አገሮች በተሻለ ፍጥነት ማደግ ይችላሉ። ታዋቂው ኢኮኖሚስት ዳኒ ሮድሪክ በቀልድ መልክ እንደሚያስቀምጡት “የኢኮኖሚ ኋላ ቀርነት አንዳንዴ ጥቅም አለው።” ሐሳቡ ቀላል ነው። ድኻ አገሮች ኃብታሞቹ የፈጠሯቸውን ቴክኖሎጂዎች በአነስተኛ ወጪ “ጉዲፈቻ” ቴክኖሎጂዎች አድርገው ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ። እዚህ ጋር አንድ ማስጠንቀቂያ ላስቀምጥ፤ ኢኮኖሚስቶች ቴክኖሎጂ የሚሉት ሐሳብ እንደ ጥቁር ጉድጓድ ያለ ኹሉንም ስቦ አስገብቶ በዚያው የሚያስቀር ነው። “ቃሉ”ን ኢኮኖሚስቶች ኀልቁ መሣፍርት ትርጉም ሰጥተውታል። መለኪያም አበጅተውለታል። ታዋቂው ብሔቪየራል ኢኮኖሚሰት ሪቻርድ ቴይለር ይህ ሐሳብ ኤተር (Aether) በሚባል ቃል እንዲጠራ ጠይቀዋል። በግሪክ ሚቶሎጂ ኤተር የገነት ሰብአዊ አምሳያ (personification) ነው። ፍጹም የሌለ ነገር። ቴክኖሎጂ ኮፒ ከማድረግ ሌላ ድኻ አገሮች ከጉልበት ዋጋ ዝቅተኝነት ይጠቀማሉ። የጉልበት ዋጋ ሲጨምር ከኢንቨስትመንት የሚገኝ ገቢ (return) ይጨምራል። ይህ ደግሞ ኢንቨስትመንትን ያበረታታል። ይህ ቀላል የዕደገት ቲዮሪ ሙሉ ለሙሉ ሐቅ ቢኾን ሁሉም አገሮች ከዐሥርት ዓመታት ጉዞ በኋላ ተመሳሳይ የእድገት ደረጃ ላይ ደርሰው ግንኙነት ይፈጠር ነበር። ይኹንና ከድህነት ተነስተው አድገው እና ተመንድገው ወደ ሀብታም አገሮች ጎራ የተቀላቀሉት ጥቂት ናቸው። ስለዚህ ደቨሎፕመንታል ኢኮኖሚስቶች የእድገት ወጋቸውን (growth story) ተጨማሪ ሐሳብ በማምጣት ያወሳስቡታል። ግንኙነትን ኹኔታዊ (conditional) እና ኹኔታዊ ያልዀነ (unconditional) ብለው ይከፋፍሉታል። ድኻ አገሮች በተለያዩ ምክንያቶች በተቋማት ደካማነት፣ በድህነት መጨመር፣ በፖሊሲ ደክመት፣ ወዘተ. . . በኒዮ ክላሲካል ኢኮኖሚክስ የተተነበየውን አባሮ የመያዝ ዕድገት ማስጀመር ይሳናቸዋል። ወይም መኪናው መንገድ ከጀመረ በኋላ ‘ሲጥ- ሲጢጥ” ብሎ ይቆማል። እነዚህ ኢኮኖሚስቶች የመሠረታዊ ልማት ግብዐቶች (developmental fundamentals) ይሏቸዋል። እያንዳንዱ ግብዐት ለልማት ያለው ድርሻ ባለሞያዎችን ያነታርካል፤ በርግጥ ኢኮኖሚስቶችን የማያጨቃጭቁ የኢኮኖሚክስ ሐሳቦች የሉም። ዴንማርካዊው ፕሮፌሰር ሞርተር ጀርቨን በቅርቡ Misunderstanding Growth in Africa: how economists get it wrong በሚል ርእስ ባሰተሙት አዝናኝ ጽሑፋቸው እንደጠቀሱት ዴቨሎፕመንታል ኢኮኖሚስቶችን በመሠረታዊ የልማት ግብዐቶች ጉዳይ እንዲስማሙ ከማድረግ ድመት ማገድ ይቀላል።

የሰር አርተር ዱዋል ሴክተር ሞዴል የኢኮኖሚ እድገትን ለመረዳት ከኒዮ ክላሲካል ኢኮኖሚክስ ቲዮሪ አንዳንድ ጊዜ ደጋፊ ሌላ ጊዜ ደግሞ አማራጭ ሐሳብ ነው። ሞዴሉ በኢኮኖሚ አወቃቀር (structure) ላይ ያተኩራል። የሞዴሉ ተከታዮች ስትራክቸራሊስት ይባላሉ። ምሁሩ ሞዴሉን ለመጀመርያ ጊዜ ያቀረቡት Economic Development with Unlimited Labour በተባለ ከታተመ በኋላ በደቨሎፕመንታል ኢኮኖሚክስ ውስጥ የስትራክቸራሊዝም ምርምርን የጎጆ ኢንዱስትሪ ያደረገ ታላቅ ሥራቸው ነው። በዚህ ሞዴል መሠረት ያላደጉ አገሮች ኢኮኖሚዎች በሁለት ይከፈላሉ። የካፒታሊስት (ዘመናዊ) ሴክተር፣ ባህላዊ ሴክተር ቲዮሪው የተተበተበ ቢኾንም ጨመቁ በቀላሉ ሲቀመጥ እንዲህ ይነበባል፤ እንደ አርሶ በልነት ያሉ ባሕላዊ ሴክተሮች ጉልበት እንደ አሸዋ የተትረፈረፈባቸው ኩርማን ምርታማነት የተጠናወታቸው ናቸው። በተቃራኒው የምርት (manufacturing) ሴክተር ምርታማነቱ ከፍተኛ ካፒታል በሰፊው የሚጠቀም፣ ከፍ ያለ ገቢ የሚገኝበት ነው። ዕድገት የሚወጣው በአርሶ በላው ሴክተር የተከማቸውን የተትረፈረፈ ጉልበት ወደ ዘመናዊ የካፒታሊስት ኢንዱስትሪ ሴክተር ሲሸጋገር ነው።

የሰር አርተር ተቺዎች በሁለት ጎራ ይመደባሉ። አንደኛው ቡድን ሞዴሉ ከነአካቴው የተሳሳተ በመኾኑ ከደቨሎፕመንታል ኢኮኖሚክስ ገጽ በፍጥነት ጡረታ መውጣት አለበት ይላሉ። ሌሎቹ ደግሞ የሞዴሉን መሠረታዊ መርኾዎቸ ተቀብለው ማሻሻያዎችን የሚያደርጉ ናቸው። የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ፖሊሲ “ጋሪውን ከፈረሱ አስቀድሟል” ሲሉ የሚተቹ እነዚህኞቹ ናቸው። ለዚህ ዕይታ የሰር አርተር ትንተና ዋነኛ ችግሮች ሁለት ናቸው። አንደኛው በልማት ምዕራፍ የመጀመርያ ገጾች በግብርና እና በኢንዱስትሪ መካከል ያለውን ጥብቅ የተደጋጋፊነት ግንኙነት ይመለከታል። ግብርናን ሳይታደጉ ወደ ኢንዱስትሪ መዝለል ከዚያ በኋላ ደግሞ ከካፒታሊሰት ሴክተር ከሚገኘው ትርፍ መካከል ከፊሉን የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ላይ አለማዋል ግብርናንም ኢንደስትሪያላይዜሽንንም ይጎዳል። ሁለቱም ከአርሶ በል ወደ ካፒታሊስቱ ሴክተር የሚደረገው የጉልበት ሽግግር ሂደት ሰር አርተር እንደሚያስቀምጡት ቁንጥጫ እና ኪሳራ የሌለው ጉዞ ሳይኾን ለአጭር ጊዜ የማያቋርጥ ስቅታ ሲያልፍ ቀሳፊ ውጋት ያለበት ነው። ሕመሙን ለመቀነስ ሽግግሩን ደረጃ በደረጃ (incremental) ማድረግ ይበጃል። ለእነዚህ ተቺዎች የግብርናን ምርታማነት መጨመርን ወደ ጎን ያደረገ የኢንዱስትሪያላይዜሽን ፕላን የኢኮኖሚ መቅሰፍት ነው። መፈክር፦ ግብርና! ግብርና! ግብርና!

It is politics, stupid!

በቅርቡ ሰር አርተር ላይ የተነበበው ትችት ከኢኮኖሚክስ ባለሞያዎች ወደ ፖለቲካ ሳይንቲስቶችም ተዛምቷል፤ በተለይ የምሥራቅ እስያን የእድገት ፖለቲካ ኢኮኖሚ በሚያጠኑት እነዚህ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች ምሥራቅ እስያ አገሮች ኢኮኖሚ ማደግ የጀመረው አርሶ አደሮች መደራጀት እና በተለያዩ መንገዶች ገዢዎቻቸው ላይ ጫና ማሳደር ሲጀምሩ እንደኾነ በማንሳት ይሟገታሉ። በጫናው ምክንያት ስር ነቀል የግብርና ሪፎርም ያደረጉ አገሮች ወደ ፈጣን እድገት ተሸጋገሩ። የግብርና ምርታማነት ማደግ በገጠር የሚኖሩ ዜጎችነ ገቢ ከፍ አደረገ፤ የምግብ ዋጋን ቀነሰ፣ ቁጠባን በማሳደጉ አነስተኛ ፋብሪካዎች ላይ የሚደረገው ኢንቨስትመንት ጨመረ። ይህ ደግሞ የፈጣን ኢንዱስትሪያላይዜሽን መሠረት ኾነ። የዚህ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ትንተና ዋነኛ አቀንቃኝ የዩኒቨርስቲ ኦፍ ላይደን ኢኮኖሚክስ እና ፖለቲካ ፕሮፌሰር ዴቪድ ሄንሊ እና በርሳቸው ስር ትናተቻቸውን የሚያደርጉ ተማሪዎቻቸው ናቸው። መልእክቱ፦ It is politics, stupid!

ከሦስት ሳምንታት በፊት በዳካር በተደረገው የአፍሪካ የግብርና ልማት ላይ ባተኮረ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በርካታ ተናጋሪዎች በእንዚህ ትንተናዎች መስማማታቸውን የሚገልጹ ወረቀቶች አቅርበዋል። ፎርሙላው ተገኝቷል፤ ጠንካራ የግብርና ሪፎርም ሲደመር የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ሲደመር መሠረታዊ የኢኮኖሚ ተቋማት እርምት እና ለውጥ ሲደመር ጥሩ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ እኩል ይኾናል የኢኮኖሚ ዕድገት ማስነሻ። ኢንዱስትሪያላይዜሽን ከዚያ ይቀጥላል። የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚያወጡ ባለሥልጣናት፣ አማካሪዎቻቸው እና የመንግሥት የልማት አቅጣጫ ደጋፊዎች በዚህ ፎርሙላ ቆርበዋል።

በርግጥ ትችቱ በዘፈቀደ መላ-ምት እና አይዲዮሎጂ ላይ ተመሥርቶ የቀረበ ሳይኾን በርካታ በጥንቃቄ የተሠሩ ምርምሮች እና በታይላንድ፣ ቻይና፣ ኮርያ፣ ታይዋን፣ ቬትናም፣ ማሌዢያ እና ጃፓን ላይ የተመረኮዘ ነው። በ1984ቱ ሌክቸር ዶክተር እሸቱ በተቀነባበረ መልኩ ባይኾንም እነዚህን ትችቶች ጣል ጣል አድረገው ነበር። ነገር ግን ከዚያ ሌክቸር ሁለት ዓመት በኋላ “ባንኛለሁ” ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት የግብርና መር ኢኮኖሚ ስትራቴጂን ሥራ ላይ አዋለ። ይህ ስትራቴጂ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ገዢ ሐሳብ ከኾነ ከ17 ዓመታት በኋላ የግብርና ምርታማነት ቢጨምርም ወደ ኢንዱስትሪያላይዜሽን የሚደረገው ሽግግር የትም አልደረሰም። የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ደጋፊዎች ለዚህ የሚሰጡት ምላሽ “ቁሌቱ ተሰርቷል፥ ምግቡን ከሚቀጥሉት ዐምሥት ዓመታት ጀምሮ ጠብቁ” የሚል ነው። ሶሻል ሳይንቲስቶች ዝግዩ ውጤት (lag effect)የሚሉት ቃል አላቸው። የአንዳንድ ፖሊሲዎች ውጤት የሚታየው ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው። በዚህ ምክንያት ተማሪዎችም ይኹኑ ፖለቲከኞች “ድንቄም የማይመስል ነገር” የሚያስብል የምክንያት ውጤት ክርክር ለማቅረብ ይችላሉ። የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያላይዜሽን እንደዚያ ይኾን? የሚቀጥሉትን ዓመታት በተስፋ እንጠብቅ ወይስ እንደ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ኢንዱስትሪያላይዜሽንም ርቆ የተሰቀለ ዳቦ ነው?

ይህን ጥያቄ ለመመለስ በግብርና ሪፎርም ተነስተው ወደ ኢንዱስትሪያላይዜሽን የተሸጋገሩ የምስራቅ እስያ አገሮችን ጉዞ እንቃኝ። በታይላንድ፣ ቻይና፣ ኮርያ፣ ታይዋን፣ ቬትናም በግብርና ምርታማነት መጨመር የጀመረበት ጊዜ እና የኢንዱስትሪው የጂዲፒ ድርሻ መነሳት መካከል ያለው አማካኝ የጊዜ ክፍተት 6.7 ዓመት ነው። የእያንዳንዱን አገር ስንመረምር ሰፋ ያለ የጊዜ ክፍተት የምንመለከተው በታይላንድ ነው፤ 8 ዓመታት። በእነዚህ አገሮች ኢንዱስትሪያላይዜሽን እና የተስፋፋውና የግብርና ምርታማነት የጨመረው መሳ ለመሳ ነው። በርግጥ ይህ ዝምድና (correlation) ብቻ ተመልክቶ እርግጠኛ የኾነ የመንስዔ ውጤት ድምዳሜ ለመስጠት ያስችላል። ለሽግግሩ ቅጽበታዊነት ሌሎች ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ይኹንና የኢትዮጵያ መንግሥት “አርዐያዎቼ” የሚላቸው አገሮች ጉዞ ካለፌት የ18 ዓመታት የኢትዮጵያ ጉዞ የተለየ እንደኾነ ቁጥሮቹ እንደወረዱ ሊቀርቡ ይችላሉ።

በቅርቡ አንዳንድ ኢኮኖሚስቶች በኢትዮጵያና በምሥራቅ እስያ አገሮች መካከል ያለው የሽግግር ክፍተት ልዩነት ከፖሊሲ እና ተግባር መዛነፍ የመነጨ ሳይዀን የተንደረበበ ኢንዱስትሪያላይዜሽን (premature deindustrialization) ከተባለ ክስተት ጋር የተቆራኘ እንደኾነ ሲገልጹ ይደመጣል። ይህን ክስተት በመጀመርያ በግልጽ ያብራሩት ዳኒ ሮድሪክ ናቸው፤ እ.ኤ.አ ከ1970ዎቹ በኋላ ፈጣን ዕድገት የጀመሩ ታዳጊ አገሮች ለኢንዱስትሪያላይዜሽን የደረሱበት ክፈፍ ከእነርሱ ቀድመው እድገት ከጀመሩ አገሮች ከደረሱበት ጣሪያ እጅግ ያነሰ ነው። ለምሳሌ ብሪታንያ የኢንዱስትሪያላይዜሽን ጫፍ ላይ ስትደርስ ምርት (manufacturing) ለሥራ ፈጠራ (employment) ያለው ድርሻ 45 በመቶ ነበር። በአሜሪካ ይህ ቁጥር 27 በመቶ ደረሰ። ደቡብ ኮርያ 28 በመቶ፣ ሜክሲኮ 20 በመቶ፣ ብራዚል 16 በመቶ፣ ቻይና 16 በመቶ፣ እያለ ጥሩ ቀስ በቀስ እየወረደ ይመጣል። ይህ ጭንጋፍ ጉዞም በነፍስ ወከፍ ገቢ ይንጸባረቃል፤ የብርታኒያ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ማሽቆልቆል የጀመረው የአገሪቱ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከስምንት ሺህ ዶላር ካለፈ በኋላ ነበር፤ ደቡብ ኮርያ 8 ሺህ፣ ሚክሲኮ 6 ሺህ፣ ብራዚል 5 ሺህ ኮሎምብያ 3 ሺህ፣ ቻይና 3 ሺህ፣ወዘተ። በአዲሶቹ አዳጊዎች የሚጀመረው ኢንዱስትሪያላይዜሽን የሚቆመው እና የሚቀለበሰው በቶሎ ነው። ለዚህ ክስተት የተለያዩ መንስዔዎች እንደ መላምት ይቀርባሉ፤ የጅምላ እድገት የሚፈጥረው ወደታች የመጎተት ፉክክር (race to the bottom) የሰው ተኪ ቴክኖሎጂዎች እያደገ መምጣት የድኻ አገሮች ጉልበት ዋጋ ዝቅተኝነት የሚያገኙትን አንጻራዊ አብላጫ (comparative advantage) ማሳጣት ወዘተ።

ምክንያቱ የትኛውም ቢኾን የተንደረበበ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ክስተት ለልማት ጀማሪ አገሮች የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነዳፊዎች ራስ ምታት ነው። ለዚህም ምክንያት አንዳንድ ኢኮኖሚስቶች “የኢንዱስትሪያላይዜሽን ማደግ የተበላ ዕቁብ ነው፤ ይህን ሞዴል መተው አለብን” እያሉ ነው። ጥያቄው ሌሎች ሴክተሮች የኢንዱስትሪን ቦታ ተክተው የእድገት አሳንሰር (growth escalator) ሊኾኑ ይችላሉ” የሚል ነው። ኢያዝ ጋሊ እና ስቴፈን ኦ’ኮነል ከአንድ ዓመት በፊት Can service be a growth escalator in low income countries? በሚል ርእስ ባቀረቡት ወርልድ ባንክ የፖሊሲ ምርመራ ወረቀት የአገልግሎቱን ዘርፍ (service sector) ሦስተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ብለው ጠርተውታል። “ የቴክኖሎጂ እድገት እና ግሎባላይዜሽን የድኻ አገሮችን አንጻራዊ ብልጫ በማሳደግ አገልግሎትን ለዓለም ገበያ እንዲያዳርሱ ያደርጓቸዋል። የአፍሪካ አምበሶች የእድገት መስመር ከእስያ ነብሮች እድገት የተለየ ነው” ይላሉ። ተመራማሪዎቹ ይህ መላምት ብቻ ሳይኾን በጠንካራ የማለዳ መረጃዎች (early evidence) የተደገፈ መኾኑን ያወሳሉ። ዳኒ ሮድሪክ በግሩም ኹኔታ እንደሚያቀርቡት የዚህ ትንተና ትልቁ ችግር የአገልግሎት ዘርፍን በአንድ ቅርጫት ውስጥ ማስገባቱ ነው። በርካታ አገልግሎቶች በዓለም ገበያ ለመሸጥ የሚያስቸግሩ (non-tradable) ናቸው። እነዚህ ደግሞ የረጋ እና የላሸቀ ከሚሉት ግብርና ብዙም ያልተሻሉ፣ አነስተኛ ገቢ የማይገኝባቸው፣ ወደሌሎች ሴክተሮች እና የኢኮኖሚ ዘርፎች መሸጋገር የሚችል የቴክኖሎጂ ቅራሪ (technological spillover) የሌላቸውን ካፒታል መሳብ የማይችሉ፤ በዓለም ገበያ ሊሸጡ የሚችሉ (tradable) የአገልግሎት ዐይነቶች ደግሞ ከፍ ያለ ብሒል (skill) የሚጠይቁ ናቸው። ይህን ለማግኘት ታዳጊ አገሮች የብዙ ዓመታት የትምህርት እና የመዋቅር ግንባታ ኢንቨስትመንት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የምርት ሴክተር ዋነኛ የልማት አሳንሰር ያደረገው ያለ ብዙ ኪሳራ በቀላሉ የአጭር ጊዜ ሥልጠና የተሰጣቸውን አርሶ አደሮች በብዛት የመምጠጥ አቅም ስላለው ነው።

የአገልግሎት ዘርፍ፥ እኩልነት፥ እና ሥራ አጥነት

በተጨማሪ በአገልግሎት ዘርፍ የተመሠረተ እድገት ለከፍተኛ ኢ-እኩልነት እና ሥራ አጥነት የተጋለጠ ነው። ለትንሽ ጊዜ ታገሱኝ እና እንደገና በኢኮኖሚክስ ሊትሬቸር ውስጥ ይዣችሁ ልለፍ፦ እ.ኤ.አ በ1950ዎቹ በታዋቂው አሜሪካዊ ኢኮኖሚስት ሳይመን ኩዝኔትስ የተተወረ “ኩዝኔትስ ከርቭ” የተባለ የእድገትን እና የገቢ ኢ-እኩልነትን የሚያሳይ መላምታዊ ግራፍ አለ፤ መላምቱ እንዲህ ይላል፦ “ አገራት ፈጣን እድገት እንደጀመሩ የገቢ ኢ-እኩልነት ይጨምራል፤ ከዚያ ያቆማል፤ ቀጥሎም መቀነስ ይጀምራል” ኩዝኔትስ ከርቭ የ “በ” ቅርጽ አለው። በቅርቡ በበለጸጉ አገሮች በአስደንጋጭ ኹኔታ እየጨመረ የመጣው የገቢ ኢ-እኩልነት የዚህን መላመት እውነተኛነት (empirical truth) ጥያቄ ውስጥ ከቶታል። በተለይ ኢማኑዔል ሻይዝ እና ቶማስ ፒኬቲ የተባሉ ኢኮኖሚስቶች እ.ኤ.አ ከ2000ዎቹ መጀመርያ አንስቶ ይህን ቲዮሪ የሚፈታተኑ እና የሚያፈራርሱ የጥናት ውጤቶችን ሲያሳትሙ ቆይተዋል።

ነገር ግን ቲዮሪውን ሊያድን የሚችል አንድ ግሩም መላምት እ.ኤ.አ በ2006 በታዋቂዎቹ ፖለቲካ ኢኮኖሚስቶች ዳረን አሲሞግሉ እና ጀምስ ሮቢንሰን ቀርቧል። ይህ መላ ምት “የፖለቲካ ኩዝኔትስ ከርቭ” ተብሎ ይጠራል። እንደ አሲሞግሉ ሮቢንሰን መላምት ከኾነ ከኢንዱስትሪያላይዜሽን እድገት ሁለተኛ ምዕራፍ ጋራ ተያይዞ የሠራተኞችን መብት ለማስጠበቅ የሚደረግ የጋራ የፖለቲካ ትግል ( collective political action) ይበረታል፣ ይጧጧፋል። ትግሉ በአብዛኛው የሚደረገው ሠራተኛውን በሚወክሉ ማህበራት እና የፖለቲካ ቡድኖች አማካኝት ነው። ከትግሉ ዒላማዎች መካከል ዋነኛው የሠራተኛውን የገቢ ድርሻ (labor’s share of income) እንዲጨምር የሚጠይቅ ነው። በታሪክ እንደምናየው ሠራተኛው በዚህ ትግል ብዙ ድሎችን አስዝግቧል። ሠራተኛው የገቢ ድርሻ ሲጨምር የገቢ ኢ-እኩልነት እየቀነሰ ይመጣል። የአገልግሎት ዘርፍ ላይ በቅርጽ እና በባሕርይው ምክንያት ለእንደዚህ ዐይነት የሠራተኛ የጋራ ትግል አይመችም።

እነዚህን እና ሌሎች አገልግሎት ዘርፍን ለዕድገት መሰላልነት የመጠቀም ችግሮችን የሚረዱ ነገር ግን የኢንዱስትሪያላይዜሽን መስመር የተዘጋ እንደኾነ የሚያምኑ አንዳንድ ኢኮኖሚስቶች ደግሞ “ትኩረት ወደ ግብርና” ኢላሉ። Employment, Unemployment and Underemployment in Africa በሚል ርዕስ ስቴፈን ጉልብ እና ፉራዝ ሀዎት ታዳጊ አገሮች የግብርና ዘርፋቸውን ዘመናዊ ካደረጉ እና ደካማ የቢዝነስ ሕጎቻቸውን ካሻሻሉ ግብርና እንደ ዕድገት አሳንሰር ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ይጠቁማሉ። ይኹንና ይሕም ሐሳብ ጥያቄ ምልክት አለበት። ምርታማነትን ለመጨመር ግብርና ከጉልበት ተኮር (labor intensive) ወደ ካፒታል ተኮር (capital intensive) መሸጋገር አለበት። ይህ ሽግግር ደግሞ በርካታ ገበሬዎችን ከሥራ ውጪ የሚያደርግ ነው።

ይህ የኢኮኖሚ መዋቅር ሪፎርምን የተመለከተ ከባድ ፈተና ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገሮች ላይ ተደቅኗል። ይኹንና የተንደረበበ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ላለፉት ኻያ ዓመታት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ያለማቆጥቆጥ እንደመንስዔ ሊነሳ አይችልም። የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያላይዜሽን አልተጀመረም እንጂ አልተጨናገፈም። በግራፍ አንድ እንደምንመለከተው የኢትዮጵያ የምርት ሴክተር ጫፍ ደረሰ ሲባል ከአገሪቱ ጂዲፒ ድርሻ 14 በመቶ ብቻ ነበር። ልብ በሉ ይህ የሥራ ፈጠራ (employment) ድርሻ አይደለም። በአንዳንድ መለኪያዎች የምርት ሴክተር መደበኛ ሥራ (formal employment) ካለው ድርሻ ከዐራት በመቶ ያነሰ ነው። ጋዳፊ “ኢትዮጵያ ገንዘብ ሳይኖራት የገንዘብ ሚኒስትር ካቋቋመች፤ እኔ የደን እና ዱር አራዊት ኮሚሽን ብመሠርት ምን ችግር አለው” ብሏል ተብሎ እንደሚቀለደው ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሚኒስትርና ለስድስት ዐሥር ዓመታት የቆየ የተሻሻለ ኢንደስትሪያል ፖሊሲ አላት እንጂ ኢንደስትሪ የላትም።

የኢትዮጵያ መንግሥት ፖሊሲ አውጪዎች ይህን አላጡትም። ስለዚህ ከተንደረበበ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ጋር የተያያዘ ክርክር ሲያሰሙ አይታይም። ይልቁንስ መልዕክታቸው “ጠብቁን!” የሚል ነው። ያለማወላወልና መዋዠቅ ግንባታዎችን በማሳደግ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ሞተር እንዳስነሱ እና ለኢንዱስትሪያላይዜሽን የሚያስፈልጉ የመዋቅር ግንባታዎችን እያደረጉ እንደኾነ ይናገራሉ። ዶክተር አርከበ ዕቁባይ Industrial Policy in Ethiopia በተባለ ጽሑፋቸው እንዳተቱት የኢትዮጵያ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ከአገሪቱ ጂዲፒ 55 በመቶ የሚኾነውን ለማኀበራዊ መዋቅር እና በቴክኒካል ስኪል ግንባታ ላይ ኢንቨስት እያደረገ ነው። መንገዶች፣ የባቡር ሐዲዶች፣ የኃይል ማመንጫዎች እየተገነቡ ነው። እንደ ዶክተር አርከበ እነዚህ እና የግብርና ልማት በጋራ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ማኮብኮቢያ ናቸው። በ2018 ኢትዮጵያ የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ማዕከል ትኾናለች።

ኢትዮጵያ ይኼን ካደረገች የኢንዱስትሪያላይዜሽን ታሪኳ ከዚህ በፊት ስኬት ካሳዩት አገሮች የተለየ ይኾናል። መጪው ጊዜ ያለፈው ጊዜ ቅጂ ነው ለማለት አይቻልም። ምናልባት ኢትዮጵያ ለሌሎች አገሮች አርዐያ የሚኾን አዲስ የእድገት አካሄድ ትከፍት ይኾናል። ይህን ለመቀበል ግን እሸቱ ጮሌ እንደሚሉት “እምነታችንን በሚበር ፈረስ ሰረገላ ላይ ማስቀመጥ አለብን።” ከዘጠኝ ዓመታቸው ጀምሮ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ከዛሬ ነገ “ሊያብብ ነው” ሲባሉ የጎለመሱት ዶክተር እሸቱ ከኀልፈታቸው ጥቂት ዓመታት በፊት “ካላየሁ አላምንም” ቢሉ የሚያስገርም አይደለም።

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: