ከሀገራችን ሰማይ ስር፡- የብሄር ብዘሀነት፣የጥቅመኝነት እና የሌብነት ኢኮኖሚ እንዲሁም መወለጃው የቀረበው ኢኮኖሚያዊ አብዮት

ክፍል አንድ

ብሄር የሚለው ሀረግ እኔ እስከማውቀው የግእዝ ቋንቋ መሰረት ያለው ሀረግ ሲሆን ትርጉሙም ህዝብ ማለት ነው፡፡ በዚህ ፅሁፍም አንባቢ ልብ ማለት ያለበት ብሄሮች ሲባል ህዝቦች ማለት ሲሆን፣ ህዝቦች ሲባል ብሄሮች ማለት መሆኑን ነው፡፡ በተጨማሪም በዚህ ፅሁፍ የብሄር ብዘሀነት ሲባል በቋንቋ፣በባህል፣ እና በአኗኗር ልዩነት የተነሳ የሚኖርን ብዘሀነትን ማእከል ያደረገ ነው፡፡ ብዙ ተባዙ የሚለው ቃል ይፈፀም ዘንድ በምንገኝበት መሬት በተሰኘችው ፕላኔት የሰው ዘር ብዛት ወደ ሰባት ቢሊዮን እየደረሰ ነው፡፡ ይህ በአራቱም የአለማችን ማእዘናት የሚኖረው ህዝብ በቋንቋ፣ በባህል ወዘተ የሚለያይ እንደመሆኑ በአንድ ሉአላዊ ሀገር የሚኖሩ ህዝቦችንም (ብሄሮችን) ሆነ በመላው አለም የሚገኙ ህዝቦችን ታሪክ በተመለከተ በዘመናዊ የታሪክ ጥናት(የዘመናዊ የታሪክ ጥናት የታሪክ አጥኚዎችን ከአንትሮፖሎጂስቶች፣ከአርኪዮሊጂስቶች፣ከሜዲካል ዶክተሮች፣ ከኢኮኖሚስቶች ወዘተ ጋር በማዛመድ አንድን ታሪክ የሚጠናበት ነው) ተጠንቶ የቀረበ ጥናት በምንገኝበት የሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ለማስረጃነቱ ከፍተኛ ዋጋ ይሰጠዋል፡፡ ወደ ፅሁፌ ትኩረት ከማለፌ በፊት ስለ ሀገራችን ብሄሮች የዘር አንድነት (በደም) በተመለከተ የራሴን እምነት እዚህ ጋር ልጥቀስ፡፡ በእኔ እምነት ለህዝቦች ዘር አንድነት ማስረጃ ከደም ትስስር (ይህ የደም ትስስር በመጋባት፣ በመወለድ ወዘተ ሊገለፅ ይችላል) በላይ ማስረጃ የሌለ እንደመሆኑ የአምስት ሺህ አመት እድሜ እና ታሪክ ባላት ሀገራችን ያሉ ብሄሮች በሀይማኖቱም ሆነ በሳይንሱ ቢታይ በደም አንድ ህዝቦች ስለመሆናቸው አዳምን እና ሉሲን በማስረጃነት ማቅረብ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ የሳይንሳዊ እና የዘመናዊ የታሪክ ጥናቶችን(የዘመናዊ የታሪክ ጥናት የታሪክ አጥኚዎችን ከአንትሮፖሎጂስቶች፣ከአርኪዮሊጂስቶች፣ከሜዲካል ዶክተሮች፣ ከኢኮኖሚስቶች ወዘተ ጋር በማዛመድ አንድን ታሪክ የሚጠናበት ነው) መነሻ በማድረግ ሳይሆን ከግሰባዊ ቁንፅል እውቀት ከሚመጣ እይታ እና ፍላጎት አኩአያ የብሄሮችን የቋንቋ እና የባህል ልዩነትን ከደም አንድነት አስቀድሞ የዘር ልዩነት አለ ብሎ ለሚያምን እና ከላይ ያቀረብኩትን የግሌን አመክንዮ አያስኬድም የሚል(ለሚል) የአዳምን (በሀይማኖታዊው) እና የሉሲን (በሳይንሳዊው) ዘር ንገረኝና ዘሬን ልንገር የሚል ጥያቄ አነሳለው፡፡

ወደ ጉዳያችን ስንገባ የዚህ ፅሁፍ ትኩረት የኢኮኖሚክስ አስተምህሮት ንድፈ ሀሳቦች ለኢኮኖሚ አብዮት ምክንያት የሚሏቸውን እና ለሀገራት የኢኮኖሚ አብዮት ምክንያት የሆኑትን ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ማእከል በማድረግ እና የብሄሮች ስብጥር ለኢኮኖሚ እድገት የአንበሳ ድርሻ አለው እንዲሁም በብሄሮች ስብጥር መነሻነት ከመጣው ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚኖርን ተቋደሽነት (በሌላ አነጋገር የሀብት ክፍፍል ፍትሀዊነት) በተመለከተ የመንግስታዊ ስርአት ላይ የተንጠለጠለ ነው በሚል የመከራከሪያ ሀሳብ በኢኮኖሚ እድገት የብዙሀኑን ህዝብ ኑሮ ሲሻሻል ተመሳጋኙ እንዲሁም ኢፍትሀዊ የሆነ የኢኮኖሚ ስርአት ለሚወልደው የኢኮኖሚ አብዮት ተጠያቂው እና መንስኤው ስርአተ መንግስቱ ነው በሚል አመክንዮ በሀገራችን መወለጃው ለደረሰው ኢኮኖሚያዊ አብዮት የገዚው ፓርቲ ፖሊሲዎች መንስኤ ስለመሆናቸው መሞገት ነው፡፡

የብሄር ብዘሀነት እና ኢኮኖሚያዊ ስርአት

የብሄር ፅንፈኝነት ለፖለቲካ አለመረጋጋት እና ለእርስ በርስ ግጭት መንስኤ ከመሆኑ ባለፈ መልኩ በኢኮኖሚ ላይ ዘለቄታዊ የሆነ አሉታዊ ተፅእኖ ይፈጥራል፡፡ በዚህም የተነሳ ሀገራት የብሄር (ethnic) ልዩነትን በኢኮኖሚ ላይ ያለውን አሉታዊም ሆነ አዎነታዊ ሚና በመፈተሽ እና በማጥነት ልዩነትን ባመቻመቸ መልኩ በፖሊሲያቸው ትኩረት እንዲሰጡት ሆኑአል፡፡ የሰው ልጅ ፍላጎት ያልተገደበ መሆኑ እንዲሁም የምድራችን ሀብት ደግሞ ውስን ከመሆኑ አኩአያ የማህበረሰቡን የብሄር ብዘሀነት መነሻ በማድረግ ብዘሀአነትን ባስተናገደ መልኩ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተነድፎ ብዙሀኑን ከድህነት ማውጣት ካልቻለ ብዙሀአነት ለኢኮኖሚ እድገት ማነቆ የመሆን እድሉ ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የእድገት ኢኮኖሚስቶች የብሄር ብዙሀአነት በአንድ በከል ከኢኮኖሚ ስርአቱ ግልጥነት እና ፍታሀዊነት (ብዙሀአነትን ከማስተናገድ አኩአያ) በሌላ በኩል የጋራ ሀብትን በተመለከተ በኢኮኖሚ ውስጥ ከሚታይ የትብብር እና የፉክክር አካሄድን ባዛመደ መልኩ እና የሰው ሀይል ለምርታማነት ካለው ሚና አንፃር መታየት እንዳለበት ይመክራሉ፡፡

የብሄር ብዘሀነት እና ኢኮኖሚያዊ እድገት

በኢኮኖሚ ስርአት ውስጥ የሚኖር ፍላጎትን እና አቅርቦትን መነሻ ያደረገ ፉክክር አምራቾችን በየጊዜው የሚለዋወጠውን የሰዎች ፍላጎት ተንተርሰው ምርቶቻቸውን በአዳዲስ ፈጠራ እንዲያጎለብቱ ሲያደርጋቸው፣ በማህበረሰብ ብዙሀአንነት ውስጥ የሚገኘው የተለያየ አውቀት፣ክህሎት የስራ ባህል ደግሞ ለ አዳዲስ ፈጠራ አጋዥ መሳሪያ ሲሆን በሌላ በከል ደግሞ በማህበረሰብ ብዙሀአንነት ውስጥ የሚኖረው የተለያየ የመሰረታዊም ሆነ የመሰረታዊ ያልሆኑ የእቃ እና የአገልግሎት ፍላጎቶች ደግሞ የ አምራቾች ፉክክር መነሻ ነው፡፡ በኢኮኖሚ ስርአት ውስጥ ያለ ጤናማ የገበያ ውድድር ብዙ አማራጮች እንዲኖር፣ የዋጋ ቅነሳ እንዲኖር እና ጥራቱን የጠበቀ እቃ እና አገልግሎት እንዲኖር ምክንያት ከመሆኑ አኩአያ ለሸማቹ የሚያበረክተው አስተዋእፆ ከፍተኛ ነው፡፡ በሌላ በኩል የገበያ ውድድር አንድ የንግድ ድርጅት ከተፎካካሪው በልጦ ለመገኘት በሙሉ አቅሙ እንዲሰራ እና የገበያ ፈጠራ ላይ እንዲያተኩር ከመርዳቱ አኩአያ ለጠቅላላው ኢኮኖሚ ያለው አስተዋእፆ ከፍተኛ ነው፡፡

በማህበረሰብ እድገት ውስጥ ትኩረት የሚደረግበት የማህበረሰብ ፍትህ እና የኢኮኖሚ እድገት ውጤት የሆነውን የገቢ (የኑሮ) መሻሻልን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ማከፋፈሉ ላይ ነው፡፡ ቡድንን መሰረት ያደረገ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሰው ሀይልን አቅም በመገንባት በመነቃቃት ላይ የተመሰረተ እንቅስቄሴ እንዲፈጠር ሲረዳ ለቡድኑ የሀብት እና የገቢ መሻሻልም ምክንየት ይሆናል ነገር ግን ፍላጎትን ከመረዳት አኩአያ፣ የማህበረሰብ እድገት ከሚያመጣው ውጤት አንፃር በብሄር ቡድንተኝነት ማቀፍ ውስጥ ያለ የሰራተኛ ሀይል በኢኮኖሚው ላይ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተፅእኖ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ይህም ማለት በአንድ በኩል ፍታሀዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል ለኢኮኖሚው ጠቃሚ የሆነውን የብሄሮችን ትብብር በማጥፋት ለማህበራሰብ አለመረጋገት ምክንያት በመሆን ለኢኮኖሚ ድቀት መንስኤ ሊሆን ሲችል በሌላ በኩል የብሄርኦችን ትብብር መሰረት ያደረገ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሰው ሀይልን አቅም በመገንባት በመነቃቃት ላይ የተመሰረተ እንቅስቄሴ እንዲፈጠር ሲረዳ ለግለሰብ የሀብት እና የገቢ መሻሻልም ሆነ ለብሄራዊ ሀብት መሻሻል ምክንየት ሊሆን ይችላል፡፡

የሰው ልጅ በቡድን መኖር ከጀመረበት ወቅት ጀምሮ በቡድን በመሆን የእለት ተእለት ህይወቱን በመተጋገዝ እና በመተባበር ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህንን የሰው ልጅን ተፈጥሮአዊ የሆነ ተሰባስቦ በቡድን የመኖር ስሜት ኢኮኖሚን መነሻ በማድረግ አሁን ወዳለንበት ዘመን ስንመልሰው፣ በአሁኑ ወቅት በአለም ላይ በየትኛውም ሀገር በቋንቋ፣ በሀይማኖት፣ በባህል፣ በአኗኗ እስታይል መመሳሰል ካለመኖሩ አኩአያ ብዙሀነትን ከኢኮኖሚ እድገትት አኩአያ ለማየት የብሄሮች ስብስብን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን መነሻ በማድረግ የብሄሮች ስብስብ ለኢኮኖሚ እድገት ያላቸውን ሚና መነሻ በማድረግ፣ የግለሰብ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለኢኮኖሚ እድገት ያለውን ሚና ከግምት በማስገባት እና በማዛመድ ይመስለኛል፡፡ እውቁ የኢኮኖሚክስ መፅሄት ዘ ኢኮኖሚስት በ ግንቦት 2005 እትሙ እንዳስነበበው ደሀ ሆነ ተወልደ ሀብታም ሆነ ልትሞት ትችላለ ነገር ግን የብሄር (የጎሳ) ማንነት በጊዜ ሂደት ውስጥ እንደማይለወጥ ይገልፃል፡፡

ያደጉ ሀገራት ተሞኩሮ እንደሚሳየን የኢኮኖሚ ስርአታቸው የማህበረሰቡን የብሄር ብዙሀነትን ባማከለ እና ልዬነትን ባጠበበ መልኩ የብሄራዊ ገቢ ክፍፍል፣የስራ እድል፣ ለኢኮኖሚው አጋዥ የሆነውን የትምህርት እድል (እውቀት) ፍታዊ በሆነ መልኩ የማህበረሰቡን የብሄር ብዙሀነት ባማከለ መልኩ ተደራሽ በማድረጋቸው አሁን ላሉበት የኢኮኖሚ ደረጃ ሊደርሱ እንደቻሉ ነው፡፡ የእቃም ሆነ የአገልግሎት ምርት ተመርቶ ከአምራቹ እስከ ሸማቹ በሚደርስበት ሂደት ውስጥ የማህበረሰቡ የብሄር ብዙሀነት በአንድ በኩል ብዙሀነት ከሚያመጣው የፈላጎት ልዩነት እና የተለያየ የስራ ባሀል ለአምራቹ የገበያ ምንጭ እና የምርታማነት አጋዥ ሀይል ሲሆን፡፡ በሌላ በኩል ነፃ እና ገለልተኛ የኢኮኖሚ ተቋማት በሌሉበት ሁናቴ ፖለቲከኞች እና ፖሊሲ አውጪዎች የብሄር ብዙሀነትን የራሳቸውን ብሄር ያማከለ የኢኮኖሚ ስርአት እንዲገነቡ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡

የብሄር ብዘሀነት ባለበት ሀገር የጥቅመኝነት ስርአተ መንግስት ውጤቱ ምን ይሆናል?

የብሄር ማንነት ኢኮኖሚ በለፀገም ፣ ደሀየም፣ ሀገር ጠነከረም፣ ተበታተነም የአንድ ብሄር አባልነት በጊዜ ሂደት ውስጥ የማይለወጥ ሆኖ ከትውልድ ትውልድ ይተላለፋል የኢኮኖሚ እድገት ደግሞ ሂደት እንደመሆኑ፣ በዚህ ሂደት ውስጥ የብሄር ብዙሀነት ለኢኮኖሚ እድገት ያለውን ሚና በማህበረሰብ ብዙሀነት ውስጥ ከባህል፣ ከአኗኗር፣ እሴት ወዘተ ልዩነት የተነሳ የሚኖረውን የተለያየ ዘውጋዊ እና አካባቢያዊ እውቀት፣ እሴት፣ ክህሎት ለኢኮኖሚ እድገቱ አጋዥ ከማድረግ አኩአያ እና የብሄር ብዙሀነትን ተንተርሰው ፖለቲከኞችና ፖሊሲ አውጪዎች ብሄርን ማእከል በማድረግ ከጥቅመኛ ባለሃብቶች ጋር በሚፈጥሩት የጥቅም ትስስር እና ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ለዘውጋቸው በሚረዳ መልኩ የኢኮኖሚ ስርአቱን በመዘወር የጠቅላላው ኢኮኖሚው ላይ ከሚያደርሱት ድቀት አንፃር ማየት ያስፈልጋል፡፡

አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ነፃ ከወጡበት እ.ኤ.አ ከ1960 ጀምሮ የኢኮኖሚያቸው ከማደግ ይልቅ የላሸቀ ሲሆን፣ ለኢኮኖሚአቸው መላሸቅም ትክክለኛ እና ግልጥ የኢኮኖሚ ስርአት አለመኖር፣ የእርስበርስ ግጭት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት ወዘተ እንደሆነ አብዛኛዎቹ ኢኮኖሚስቶች ተደጋጋሚ በሆነ ሁኔታ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ሮበርት ባሮው ለተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ እድገት ማነቆዎች ላይ ጥናት ባደረገበት Determinants of Economic Growth: A Cross-country Empirical Study በተባለው ጥናታዊ ፅሁፉ፣ ለአፍሪካ ሀገራት የድህነት እና ዘላቂ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ላለማምጣታቸው ምክንያት አብዛኛዎቹ ኢኮኖሚስቶች ከገለፁት በተጨማሪ የጎሳ (ethnic) ቡድንተኝነት ማእቀፍ የኢኮኖሚ ስርአቱን በጎሳ ጥቅመኝነት ላይ የተገነባ እንዲሆን ስላደረገው የኢኮኖሚ እንቅስቃሲዎቻቸው በፉክክር ላይ የተመሰረተ እንዳይሆን ማነቆ መሆኑን በመግለፅ የአፍሪካ አንባገነን መንግስታት የብሄር ብዘሁአንነት የብዙሀኑን ህዝብ ኑሮ ለሚያሻሽል ኢኮኖሚያዊ እድገት ግብአት ከማድረግ ይልቅ የጎሳ (ethnic) ቡድንተኝነትን ለወንበራቸው ማስጠበቂያ በማድረጋቸው የተነሳ ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ድቀት መንስኤ መሆኑን በኢኮኖሚክስ ንድፈ ሀሳብ በማስደገፍ ይሞግታል፡፡

   አብዛኛዎቸ የሶስተኛው አለም ሀገራት የኢኮኖሚ ስርአታቸው አብዛኛውን ህዝባቸውን ከድህነት ላለማውጣታቸው ከሚነሰት ምክንያቶች አንዱ በፖሊሲ አውጭዎች እና በአምራቾች መሃል ባለ የጥቅመኝነት ትስስር የተነሳ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻቸው አብዛኛውን ህብረተሰብ ተደራሽ ማድረጉ ቀርቶ ጥቂት ተሞዳማጅ ባለሃብቶችን ማእከል ባማድረጉ ምክንያት ነው፡፡ በኢኮኖሚ ስርአት ውስጥ በፖሊሲ አውጭዎች እና በአምራቾች መሃል የጥቅመኝነት ትስስር ከሚፈጥሩ ምክንያቶች አንዱ በኢኮኖሚ ስርአት ውስጥ የሚፈጠር ቋንቋን፣ ሀይማኖትን፣ ባህልን ወዘተ ማእከል ያደረገ የፖሊሲ አውጪዎች እና የባለሀብቶች የጥቅመኝነት ትስስር (ቡድንተኝነት) ነው፡፡

   እውቁ ኢኮኖሚስት ሮበርት ባሮው ግልጥነት በሌለው የኢኮኖሚ ስርአት ውስጥ ስልጣኑን የጨበጡት ፖሊሲ አውጪዎች ኢኮኖሚውን ከሚዘውሩት ባለሀብቶች ጋር ብሄርን ማእከል ያደረገ የጥቅም ትስስር የሚያደርጉበት እድል ከፍተኛ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ በተለያየ ልዩነት ላይ የቆመ (በቋንቋ፣ በባህል፣ በሀይማኖት ወዘተ) ህብረተሰብ በሚበዛበት ማህበረሰብ ያለ ልዩነት ከቆመ (በቋንቋ፣ በባህል፣ በሀይማኖት ወዘተ) ህብረተሰብ አንፃር ሲታይ ከደካማ እና ዘውግን ማእከል ባደረገ የጥቅመኝነት አስተዳደር የተነሳ ለኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች የመጋለጥ እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ነገር ግን በተለያየ ልዩነት ላይ የቆመ ህብረተሰብ በራሱ ለኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች ምክንያት ነው ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በቋንቋ፣ በባህል፣ በሀይማኖት ወዘተ የተለያዩ ህብረተሰቦች በሚኖሩበት ሀገራት የሀብረተሰቦች ልዩነቶች ለኢኮኖሚው እድገት ምሶሶ መሆናቸውን ከማሳየታቸው አንፃር የማህበረሰብ ልዩነት በራሱ የኢኮኖሚ እድገት ማነቆ አለመሆኑን እና ከ ማህበረሰብ ልዩነት ልዩነት ይልቅ የኢኮኖሚ ስርአቱ ግልጥነት አለመኖር የማህበረሰብ ልዩነትን ተጠቅመው ፖሊሲ አውጪዎች እና ፖለቲከኞች ከባለሀብቶች ጋር ብሄርን መሰረት ያደረገ የጥቅመኝነት እና የአድርባይነት ትስስር መፍጠራቸው መሆኑን ማሳያ ነው፡፡

   በአሁኑ ወቅት የቴክኖሎጂ መስፋፋት እና ግሎባሊይዜሽን በአንድ በከል የአምራች እና የሸማቹን የገበያ ልውውጥ አከሃኤዱን በየጊዜው መልኩን እንዲለዋውጥ ሲያደርገው በሌላ በኩል የተለያዩ ሀገራት ባለሀብቶች ከሀገራቸው አልፈው በሰው ሀገር መዋእለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ምክንያት ሆናቸዋል በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ሀገራት ግልፅ የሆነ የኢኮኖሚ ስርአት መዘርጋት ግዴታ እየሆነባቸው መጥቷል፡፡ በኢኮኖሚ ስርአት ውስጥ ያለው የአምራች እና የሸማች ትስስር በአጠቃለይ የኢኮኖሚው ፖሊስ ስር የተንጠለጠለ እንደመሆኑ በፖሊሲ አውጭዎች እና በአምራቾች መሃል ያለ የጥቅመኝነት ትስስር ኢኮኖሚውን ውድድር አልባ በማድረግ የሞኖፖሊ ስርአት እንዲሰፍን በማድረግ ሀገር በደለቡ ፖሊሲ ሰራቂ ባለሃብቶች ስር እንድትወድቅ ከማድረግ ባለፈ ለኢኮኖሚያዊ አብዮት መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡

በኢኮኖሚ ስርአት ውስጥ የፖሊሲ አውጪው ሚና አብዛኛውን ማህበረሰብ ተደራሽ ባደረገ መልኩ ድህነትን ቀራፊ የሆኑ ፖሊሲዎችን ከፖለቲካው ክበብ ነፃ ከሆኑ ተቋአማት ጋር በመተባበር መንደፍ እና መተግበር ነው፡፡ የአብዛኛዎቹ ደሀ ሀገራት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻቸውም ከጠረቤዛ ያልዘለለ ፋይዳ እንዲኖራቸው ያደረጋቸው የሚነደፉት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በወረቀት አብዛኛውን ማህበረሰብ ተደራሽ ሲያደርጉ በተግባር ግን ጥቂት ህብረተሰብን በተለይ ለፖሊሲ አውጪው እና ለፖለቲከኛው ቅርብ የሆኑ ግለሰቦችን እና ባለሃብቶችን ተደራሽ ማድረጋቸው ነው፡፡ በኢኮኖሚ ስርአት ውስጥ የሚፈጠር ብሄርን ማእከል ያደረገ የጥቅም ትስስር በተለይ ውስን የሆነ የመንግስት በጀት እና ብዙሀኑ ህብረተሰብ ከድህነት ወለል በታች በሆኑባቸው ደሀ ሀገራት ኢኮኖሚውን ከማመሳቀሉ በላይ በህብረተሰቡ ውስጥ ከሀብት ክፍፍል፣ ከስራ እድል ጋር ተያይዞ ለሚከሰተው ለኢኮኖሚያዊ አብዮት መንስኤ ስለመሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

ይቀጥላል …..

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: