ድርቁ ፣ ነፃ ሚዲያን የሚጠላው መንግስታችን እና ፋክት መፅሄት

MY SITE LOOOOGO BEST ONE

በዚህ ፅሁፌ ረሀብን ታሪክ ያደርጋል በተባለለት በአምስት አመቱ የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን መገባደጃ ላይ በሀገራችን በተከሰተው ድርቅ የተነሳ የተከሰተውን የምግብ እጥረት መቋቋም ያልተቻለው ገዢው ፓርቲ ከሀያ አመት አገዛዝ በሁአላ እንኳ የነደፋቸው ፓሊሲዎች ነፃ ሚዲያዎችን ከሀገሪቷ ከማጥፋት በቀር በሀገሪቷ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ባለመቻላቸው የተነሳ ስለመሆኑ ገዢው ፓርቲ የአምስት አመቱ የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ይፋ ባደረገበት ወቅት የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ እቅዱን አስመልክቶ በግፍ በተዘጋችው ፋክት መፅሄት ላይ ያቀረበውን ፅሁፍ በድጋሚ እንደመከራከሪያ በማቅረብ እሞግታለው፡፡

የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ፖሊሲ ምንነትና ተግባራዊ የመሆን ችግር!

የዕድገትና የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ ከረዥም ጊዜ አኳያ የአነፃፀረውን ዋና ዓላማ በሁለት መሰረታዊ ነገሮች ያስቀምጣቸዋል። ይህም በምእራፍ 2 በገጽ ሰባት ላይ ከታች በተመለከተው መልክ ሰፍሯል።

Ethiopia`s long-term vision is

“to become a country where democratic rule, good-governance and social justice reigns, upon the involvement and free will of its peoples; and once extricating itself from poverty and becomes a middle-income economy.”

Its vision in the economic sector is

“ to build an economy which has a modern and productive agricultural sector with enhanced technology and an industrial sector that plays a leading role in the economy; to sustain economic development and secure social justice; and, incrase per capita income of citizens so that it reaches at the level of those in middle-income countries.”

የዕቅዱ ዋና የረዥም ጊዜ ዓላማ እንደዚህ ቁልጭ ብሎ ከተቀመጠ፣ በ ኢህአዴግ በተለያዩ ጊዜ የተነደፉትን የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች እና ውጤታቸው እንዳለ ሆኖ ይኸኛውንስ ተግባራዊ ሊያደርግ የሚያስችለው ፍላጎትና የሚመራበት ፊሎሶፊ አለው ወይ? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። መንግስት በዚህ የረዥም ጊዜ ዓላማ ብሎ በነደፈው ውስጥ የማዕከለኛ ገቢ አላቸው የሚባሉ አገሮች እስካሁን ኢህአዴግ የሙጥኝ ብሎ የተጓዘበትን መንገድ ይዘው ነው ሊደርሱና ብሄራዊ ኢኮኖሚ ሊገነቡ የቻሉት ወይ? ሲነሱስ ብሄራዊ አጀንዳቸው ምን ነበር? አገራቸውን በክልሎች በመከፋፈልና ርዕይ እንዲያጡ በማድረግ ነው ወይ ወደ ማዕከላዊ ገቢ ኢኮኖሚ ሊያመሩ የቻሉት? ብሎ መጠየቅም ተገቢ ይመስለኛል።

ትራንፎርሜሽን ማለት ሁለንታዊ ለውጥ ማለት ነው። ወደ ህብረተሰብ ሲለወጥ ለምሳሌ የፊዩዳሊዝምን ወደ ካፒታሊዝም መሸጋገር ወይም መለወጥ መመልከት ይቻላል። በዚህ ረገድ በስድሳኛውና በሰባኛው ዐመተ ምህረት የፊዳዩሊዝምን ወደ ካፒታሊዝም መሽጋገር የጦፈ ክርክርና ጥናት ተካሂዷል። ለማንኛውም ስልትራንስፎርሜሽን ስናወራ፣ ማቴሪያላዊ፣ ሃሳባዊና መንፈሳዊ፣ ተቋማዊና ሌሎች ነገሮችን፣ ለምሳሌ እንደ ትምህርት የመሳሰሉትንም የሚያካትት መሆን አለበት። በታሪክ እንደታየው ካለ ሬናሳንስ፣ ካለ ሪፎርሜሽንና ካለ ኢንላይትሜንት እንቅስቃሴ፣ ከዚህም ባሻገር ካለሳይንስና ካለቴክኖሎጂ ግኝት ትራንስፎርሜሽን ሊኖር እንደማይችል የአውሮፓው ታሪክ ያሰተምረናል። ይህ ብቻ ሳይሆን የአውሮፓን ታሪክ ላነበበ፣ መጀመሪያ እንዱስትሪዎች እዚህና እዚያ ከመተከላቸው በፊት፣ በጊዜው አይቻልምም፣ በመጀመሪያ ደረጃ የሚያማሩ ከተማዎችን መገንባት፣ የዕደ-ጥበብ ሙያዎችንና ንግድን ማስፋፋት፣ ትላልቅ ቤተክርስቲያናትንና ቤተመንግስቶችን መስራት ለለውጥ አመቺ ሁኔታ እንደፈጠሩ ምርምሮች ያረጋግጣሉ። እነ ኮፐርኒከስና ጋሊሌዮ በተዓምር የተፈጠሩ ሰዎች ሳይሆኑ በጣም አመቺው ሁኔታ የፈጠራቸው ናቸው። በዚህ ላይ በጊዜው በአዳዲስ ስራዎች የተማረኩ ነገስታት ለሳይንስና ለለውጥ አመቺ ሁኔታዎች ፈጥረዋል። ወደ እንግሊዝም ስንሄድ ፍራንሲስ ባኮንና ኒውተን ካለምክንያት የተፈጠሩ አይደሉም። አመቺው ሁኔታ የወለዳቸውና ሁኔታውን በመጠቀም ጥልቅ ምርምር በማድረግ ለኛ ሁሉ የሚሆን የሳይንስ ግኝት ያደረጉ ታላላቅ ሰዎች ናቸው።

ከዚህ ስንነሳ የኢህአዴግ የትራስፎርሜሽን ፖሊሲ እጅና እግር የሌለው ነው። ዝም ብሎ አስፈላጊውን የምሁራዊ እንቅስቃሴ እርምጃና ሁለንታዊ የሆነ የኢንስቲቱሽን ግንባታ ሳያካሄድ እንዲያው በአየር ላይ የሚካሄድ ይመስል ዝም ብሎ የሚወራ ፕሮፖጋንዳ ነው ። ትራንስፎርሜሽኑ በአዲስ ሰዎችና አዲስ ሃሳብ ባለቸው፣ እንዲሁም ፍላጎትን በተላበሱ ሊካሄድ የታለመ አይደለም። ሃያ ዐመት ያህል ሀገራችን መዝረፋቸው ሳያንስ በነዚሁ ዘራፊ ሰዎች ነው እንዲካሄድ የታሰበው። ይህ ብቻ አይደለም፤ በዕድገትና በትራንስፎርሜሽን ታሪክ ውስጥ ከውጭ የሚመጣ አሳብና መዋዕለ-ነዋይ አስፈላጊ ቢሆንም፣ በታሪክ ውስጥ እንደታየው የአንድ አገር ዕድገት ተሸካሚና አራማጅ ኃይል የአገሬው ህዝብ ነው። ከውጭ የሚመጡ ኢንቬስተሮች-በጊዜው ይህ ቃል አይታወቅም ነበር- እዚያው አገር ውስጥ ለመኖር የሚችሉና ለጠቅላላው ኢኮኖሚና የህብረተሰብ ዕድገት አስተዋፅዖ ማድረግ የሚችሉ ነበሩ፤ መሆንም አለባቸው። በጣሊያን በ13ኛው ክፍለ-ዘመን፣ በእንግሊዝ በ16ኛውና በ17ኛው ክፍለ-ዘመን፣ በጀርመን ደግሞ በ18ኝውና በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ከውጭ አዋቂዎችንና የዕደ-ጥበብ ሰራተኞችን እያስመጡ ማስፈርና ህብረተሰብአዊ አካል እንዲሆኑ ማድረግ የተለመደ አሰራር ነበር። ስለዚህም እነዚህ ከውጭ የመጡ ኃይሎች የበላይነት ሳይሰማቸው አጠቃላይ የሆነ የህብረተሰብ ሀብት ለመፍጠር ችለዋል። ወደ ሀገራችን ስንመጣ ግን ኢንቬሰተሮች እየተባሉ የሚገቡትና ካራቱሬን የመሳሰሉ ትላልቅ የእርሻ መሬቶች የሚሰጣቸው ንጹህ ዘራፊዎች ናቸው። ፀረ-ዕድገቶች ናችው። ህብረተሰብ እንዳንመሰርትና የቴክኖሎጂ ባላቤት እንዳንሆን የሚያደርጉን ናቸው። ተበጣጥሰንና ብዥ ብሎብን እንድንኖር የሚያደርጉን ናቸው። በስነ-ስርዓት የሚደራጅ ባህላዊና ለጠቅላላው ህዝብ የሚጠቅም የኢንዱስትሪ ፖለቲካ እንዳይካሄድ እንቅፋት የሚፈጥሩ ናቸው። ህብረተሰብአዊ ሰንሰለትና ልዩ ዐይነት ባህል እንዳይዳብር የሚያግዱ ናቸው። በዘለዓለማዊ ድህነት እየማቀቅንና እየተሳቀቅን እንድንኖር የሚያድረጉን ናቸው። ነፃነታችንና ማንነታችንን የሚገፉ ናቸው። በመሬታችንና በተቀደሰቺው ተፈጥሮአችን ላይ ዘመቻ የሚያደርጉ ናቸው። ዛፎቻችን እንዲቆረጡ፣ ውሃዎቻችን እንዲመረዙና፣ በጠቅላላው የአካባቢ ሁኔታ እንዲዛባ የሚያደርጉ ናቸው። በዚህ መልክ እንደእኔ እምነት ሳይንስና ቴክኖሎጂዎችን መቀዳጀትና ማዳበር በፍጹም አይቻልም።

በተጨማሪ የመንግስት የትራንስፎርሜሽን ፖሊሲ ከየት ወደየት እንደሚወሰደን አይነግረንም። ያለንበት ስርዓትም ምን እንደሆን አይነግረንም። ዝም ብለን ብቻ መኪና ውስጥ ገብተን እንጓዝ ነው የሚለን። ወደ ካፒታሊዝም ነው፣ ወደ ገበያ ኢኮኖሚ ወይስ ወደ ሶሻሊዝም የሚወስደን። ይህ ግልጽ እስካልሆነ ድረስ አስር ጊዜ የተለያየ ስም እየተሰጠው የሚወጣ ፖሊሲ የባሰ ውዥንብር ውስጥ ነው የሚከተን። ስልጣን በያዙ የመጀበሪያው አስር አመት ጊዜ የመንግስት ባለስልጣኖች እና ፖለቲከኞች ጀርመን ለጉብኝት ሲሄዱ መንግስት የሁሉኑም አገር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከመረመረና ካየ በኋላ አሁን የጀርመኑን ሞዴል ለመከተል እንደወሰነ ሲያወሩ ከጥቂት ዐመታት በኋላ ከቻይና መንግስት ጋር ሽር ጉድ ሲባል ደግሞ የቻይናውን መንገድ ነው የምንከተለው ሲሉ፣ ይህ ሳይባቃ በ 2004 ስለ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የሁለት ዐመት ተኩል ውጤት ገለጻ የሰጡት የገንዘብና የልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድ የደቡብ ኮሪያውን ሞዴል ነው ለመከተል ያሰብነው አሉን። ይህ የሚያመልክተው ከፍተኛ ውዥንብርና የምሁር ክፍተት እንዳለ ነው። ፖሊሲ አውጭዎቹ ምን እንደሚሰሩ አያውቁም ማለት ነው።

በእኔ እይታ ፖሊሲው በኢኮኖሚው ረገድ አሁንም ኢሀአዴግን እና ፍርፋሪ ለቃሚዎቹን የኢኮኖሚ የበላይነት የሚያጠነክር ነው። በምንም ዐይነት መልኩ በነፃ ለመንቀሳቀስ የሚፈልጉና ጊዜ የሚጠባበቁ የአገር ቤት ኢንቬስተሮች መፈናፈኛ የሚሰጥ አይደለም። የውስጥ ገበያ እንዲስፋፋና እንዲገነባ የሚያግዝ አይደለም። አሁንም ኢትዮጵያ የቡና፣ የስኳርና የሰሊጥ አምራች በመሆን ለኢንዱስትሪ አገሮች የጥሬ-ሀብት አቅራቢ ሆና እንድትቀር የሚያደርግ ነው። ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ያሉትን የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ስንመረመር በክልሎች መሀከል ትልቅ ልዩነት እናያልን። ዘጠና በመቶ በሚሆነው የአገሪቱ ግዛት ውስጥ ዘመናዊ የሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሲካሄድ አይታይም። የልማትና የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ በየክፍለ-ሀገራቱ ምን ምን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እንዳሉና እነሱንም እየተዘዋወሩ የጎበኙና የሚጎበኙ አይደሉም። ለምሳሌ ብዙዎች የድሮዎቹ የክፍለ-ሀገራት ከተማዎች ወደ መንደርነትና ወደ ጫት መቃሚያነት መለወጣቸው የፈጠጠ ሀቅ ነው። ቢሮዎች የመመራመሪያና የፖሊሲ አውጭ መስሪያቤቶች ከመሆን ይልቅ ወደጨአት መቃሚያነት ተለውጠዋል። በየአካባቢው ዕድገትንና ትራንስፎርሜሽንን የሚያግዙ ዘመናዊ ተቋማት ባለመተከላቸው ብዙሀኑ ህብረተሰብን ወዴት እንደሚጓዝ ግራ የገባው ይመስላል። ባጭሩ ዛሬ ኢትዮጵያችን በፍጥነት ወደ ማዕከለኛው ዘመን የምትጓዝ አገር ለመሆኗ የአገሪቱ ሁኔታዎች በገሃድ ያረጋግጣሉ። ስለሆነም ዛሬ በመዝናናት ስለ ዕድገትና ትራንፎርሜሽን የምናወራበትና የምንደልቅበት ዘመን ሳይሆን፣ ሀዘን የምንቀመጥበትና፣ እየፀለይን እግዚአብሄርን የምንማፀንበት ወቅት ነው።

ማጠቃለያ

ገዢው ፓርቲ ከሀምሳ እና ስልሳ አመታት በፊት የአሜሪካ ፖለቲከኞች ያመኑትን የግል ፕሬሶች ለመንግስት ሶስተ|ኛ አይን የመሆናቸው እውነትነት ከስልሳ አመት በሁአላ እንኳ ያልገባው እና እንዲገባው የማይፈልገው ገዢው ፓርቲ የገዢው ፓርቲ አዙሪት ሀገሪቷን ወዴት እየወሰዳት ስለመሆኑ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ከ ሁለት አመት ከሶስት ወር በፊት በገዢው ፓርቲ በተዘጋችው ፋክት መፅሄት የአምስት አመቱን የእድገት እና የትራንስፎርሜሽን እቅድን አስመልክቶ ያቀረበው መከራከሪያ አሁን ላይ ፋክት መፅሄት ከመዘጋቷ እና ከአስራ አምስት ሚሊዮን ህዝብ በላይ በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ በተከሰተው ድርቅ ለከፋ የምግብ እጥረት ከመጋለጡ ጋር ስንገምደው ከሁለት አስርት አመታት አገዛዝ በሁአላ እንኳ ነፃ ሚዲያዎችን ከሀገሪቷ ከማጥፋት በቀር በሀገሪቷ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ስለአለመቻሉ የሚያመላክት ይመስለኛል፡፡

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: