ልማታዊ መንግስት እና ኢህአዴግ

የዲሞክራቲክ መንግስት ግቡ እንደማህበረሰብ የተማረ፣ኢኮኖሚዊአዊ ፍላጎቱ የተሟላለት እንዲሁም በፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ህይወቱ ከማንም ተፅእኖ ውጪ ነፃ የሆነ ሙሉ ዜጋ መፍጠር ሲሆን ይህን ግቡን ለማሳካት ደግሞ እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚቀመጠው በአንድ ሉአላዊ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ህዝቦችን ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አቅምን በማቀናጀት የሀገርን አቅም የሚገነባ አምራች ሀይል በመገንባት ልማታዊ ሀገር መፍጠር መቻሉ ነው፡፡ ልማታዊ ሀገር ሲባል መንግስታት ከህዝብ ያገኙትን የማስተዳደር ውክልና ተጨባጭ ለሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመንደፍ እና ለፖለቲካ ስርአቱ አጋዥ እንጂ ፍትሀዊ ባልሆነ መልኩ ወገንተኛ ያልሆኑ ነፃ እና ገለልተኛ የሆኑ ገበያ ፈጣሪ ፣ ገበያ ተቆጣጣሪ ፣ገበያ አረጋጊ፣ ኢኮኖሚው ላይ ተሳታፊ የሆኑትን ዋስትና የሚያረጋግጡ እና ግጭት የሚፈቱ የኢኮኖሚ ተቋአማትን በኢኮኖሚ ስርአቱ ተሳታፊ በማድረግ የኢኮኖሚ ስርአቱን በትክክለኛ አቅጣጫ በማስኬድ አብዛኛውን ህብረተሰብ ተደራሽ ያደረገ የኢኮኖሚ እድገት የሚያስመዘግቡበት ሀገር እንደማለት ነው፡፡ የሁለተኛው የአለም ጦርነትን ማለቅን ተከትሎ አለም በፖለቲካ አይዶሎጂ የተነሳ ለሁለት መከፈሉ በሀገራት የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ ከጦርነቱ ፍፃሜ በሁአላ ለአራት አስርት አመታት ጥላውን አጥልቶ በነበረበት ወቅት የምስራቅ ኤሽያ ሀገራት መንግስታት (በተለይ ጃፓን) ኢኮኖሚያቸውን በማሻሻል የህዝባቸውን የኑሮ ደረጃ ከፍ ማረግ ችለው ነበር፡፡ ምንም እንኩአ ስለ ልማታዊ መንግስት ሲወሳ የጃፓን እና የምስራቅ ኤሽያ ሀገራት መንግስታት ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በሁአላ በሀገራቸው ለኢንደስትሪ መስፋፋት ከተጫወቱት የላቀ ሚና ጋር በተዛመደ መልኩ ቢሆንም እንኩአ ልማታዊ መንግስት እና ከ ልማታዊ መንግስት ጋር የተዛመዱ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ በማድረግ ጃፓን እና ምስራቅ ኤሽያ ሀገራት መንግስታት ግን የመጀመሪያዎቹ እና ብቸኛዎቹ ሀገራት አልነበሩም ምክንያቱም የላቲን አሜሪካ ሀገራት የሁለተኛው ጦርነት ከተጠናቀቀበት እስከ 1960ዎቹ፣የአውሮፓ ሀገራት በ17 ኛው እና 18ኛው ክፍለዘመን እንዲሁም አሜሪካ በ 19 ክፍለዘመን የልማታዊ መንግስትን ፖሊሲ ተግባራዊ ያደርጉ ነበርና፡፡

ልማታዊ መንግስት ስንል

ልማታዊ መንግሰት መንግሰታት በኢኮኖሚው ላይ ባላቸው ጣልቃ ገብነት እና የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት በሚሄሩበት የፖሊሲ አቅጣጫ መንግሰት ባለው ሚና ይገለፃል፡፡ በልማታዊ መንግስት ንድፈሀሳብ አንኩአሩ እና ትኩረት የሚሰጠው መንግስታት ለ ኢኮኖሚያዊ እድገት በሚሰጡት ትኩረት እና መንግስታት የኢኮኖሚ እድገትን ለማቀላጠፍ እና ኢኮኖሚያቸውን ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ ለማሸጋገር በኢኮኖሚው ላይ በሚኖራቸው የተመጠነ ጣልቃ ገብነት ላይ ነው፡፡ ቦለስታ China as a Developmental State በተባለው ጥናታዊ ጥሁፉ የልማታዊ መንግስት ኢኮኖሚ ስርአት በነፃ የኢኮኖሚ ስርአት እና የእዝ ኢኮኖሚ በሚታይበት የኢኮኖሚ ስርአት መሀል ያለ መሆኑን ያወሳና በካፒታሊስት እና በሶሻሊስት መሀል ያለ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ስርአት መሀል ያለ መሆኑን ይገልፃል፡፡ አሁን ባለንበት የ 21 ክፍለ ዘመን የልማታዊ መንግስት የኢኮኖሚ ስርአት ላይ ያለው ሚና ኢኮኖሚውን ልክ እንደ እዝ ኢኮኖሚ መቆጣጠር ሳይሆን ለፖሊሲው ተፈፃሚነት ብቻ ሲባል የቁጥጥር ስርአት በመዘርጋት ተጨባጭ የሆነ የአጠቃላይ ኢኮኖሚ ፖሊሲ በመንደፍ ለኢኮኖሚ እድገት አጋዥ የሆኑትን መሰረተ ልማቶች በማስፋፋት (መንገድ መስራት፣የሀይል ማመንጫ መገንባት ወዘተ የልማት ወይም የኢኮኖሚ እድገት ግብአት እንጂ በራሱ ብቻውን ልማት አይደለም) ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት በማምጣት እንዲሁም ሰዋዊ የሆኑ ልማቶችን (ለማህበረሰብ እድገት አጋዥ የሆኑትን ት/ቤቶች፣ዩኒቨርስቲዎች ወዘተ) በማስፋፋት የአብዛኛውን ህብረተሰብ ኑሮ ማሻሻል ላይ ማተኮር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በልማታዊ መንግስት ንድፈ ሀሳብ መሰረት የልማታዊ መንግስት ትልቁ ትኩረቱ የማህበረሰቡን ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፍላጎቶች ማማላት ነው፡፡
ኢሃአዴግ ከልማታዊ መንግስትነት አኩአያ

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ድንገት ከ 1997 አ.ም ሀገራዊ ምርጫ በሁአላ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በድንገት ልማታዊ መንግስት መሆናቸውን ካወጁ ጀምሮ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ስለ ልማት እና ልማታዊ መንግስት በስልጠና፣በሴሚናር በሚዲያ አትኩሮ በመንገር እና በማሳወቅ ላይ ያተኮረ ሲሆን በሌላ በኩልም የ ልማታዊ መንግስትን ሀሳብ የፓርቲው የሁሉም ንድፈ ሀሳብ መነሻ አድርጉአል፡፡ ስለ ኢህአዴግ ፓርቲ የልማታዊ መንግስትነት የአቶ መለስ ዜናዊን ( ኦፊሻል ያልሆነ) የዶክትሬት ዲግሪ ማማያ ጥናታዊ ፅሁፍ የሆነውን African Development the dead ends and the new beginning ባገናዘበ መልኩ የልማታዊ መንግስትን ንድፈ ሀሳብ መነሻ በማድረግ የኢሃዴግን ልማታዊ መንግስትነት እራሱ ኢህአዴግ ችግሮቼ ከሚላቸው (የፅሁፉ ትኩረት የልማታዊ መንግስት ንድፈ ሀሳብ እና የ ኢሃዴግ ፓርቲ ስለሆነ የልማታዊ መንግስትን ንድፈ ሀሳብ እና የኢትዮጲያ ነባራዊ ሁነታ ላይ ትኩረት አያደርግም) በመነሳት ተግዳሮቶቹን (ተቃርኖዎቹን) ማየት ተገቢ ይመስለኛል ፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ African Development the dead ends and the new beginning በተባለው (የያንዳንዱ ምእራፍ ሀሳብ አጠር አጠር ተደርጎ በየምእራፉ ተከፋፍሎ ለንባብ እንዲበቃ የተደረገ ነው) የዶክትሬት ዲግሪ ማሙአያ ጥናታዊ ፅሁፍቸው የአፍሪካ ሀገራት ችግር የልማት ችግር መሆኑን በመጥቀስ የስከዛሬው የኒኦሊበራሊዝም አካሄድ ደግሞ ለአፍሪካ ሀገራት ልማት እንቅፋት መሆኑን በማውሳት ኒዮሊበ ራሊዝም በአፍሪካ ጊዜው እንዳለፈበት ይሞግቱና አሁን አፍሪካ ልማት (የኢኮኖሚ እድገት) ለማምጣት ተጨባጭ እና ቀጣነት ያለው ፖሊሲ እነደሚያስፈልጋትና ፖሊሲን ደግሞ የሚተገብር ለረዥም ጊዜ (ፖሊሲውን ከመተግበር አኩአያ) የሚቆይ ልማታዊ መንግስት (ፖሊሲ አውጪ እና አስፈፃሚ እንደመሆኑ) እንደሚያስፈልግ በማውሳት ልማታዊው መንግስት ደግሞ ብቁ የሆኑ ባለሞያዎችን ይዞ ፖሊሲውን ማስፈፀም እና የማህበረሰቡን የኢኮኖሚ ችግሮች መፍታት ለረዥም ጊዜ በስልጣን ለመቆየቱ ዋስትናው እንደሆነ ሞያዊ ሃሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በአሁኑ ወቅት የአመራሩ እና የአባላቱ አድርባይነት፣ አቶ አዲሱ ለገሰ ሰሞኑን በፓርላማ ቀርበው እንደገለፁት የክልሎች የማስፈፀም ብቃት አናሳነት፣ በገዢው ፓርቲ ስር ያሉት ተቋማት የማስፈፀም ብቃት አናሳነት (የሰሞኑ የራዲዮ ማስታወቂያ የቴሌ፣መብራት ቕንጅት አልባ አሰራር ማመላከቱን ልብ ይሉአል)፣ የአባላቱ የንድፈ ሀሳብ እውቀት አናሳነት ለፓርቲው ፖሊሲ ትግበራ ውስጣዊ ችግሮቼ በማለት ይገልፃቸዋል፡፡ እንደ እኔ እምነት ትልቁ ጥያቄ የምለው የልማታዊ መንግስትን ንድፈ ሀሳብ ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ባዛመደ መልኩ ለመተግበር ቀብድ ከሆኑት ውስጥ ዋነኞቹ ለኢሃዴግ ተግዳሮቶች ከሆኑ የኢሃዴግን ልማታዊ መንግስትነትን ወላፈንዲ አያደርገውም ወይ የሚለው ነው፡፡
ከልማታዊ መንግስት አላማዎች አንዱ መሰረተ ልማቶች ባልተስፋፉበት ለኢኮኖሚው አውታር ለሆኑት ለግብርና እና ለኢንደስትሪ ክፍለ ኢኮኖሚዎች ምቹ በሆኑት አካባቢዎች መሰረተ ልማት ማስፋፋት እና ለባለሀብት ምቹ ማድረግ ሲሆን ይህን ለማሳካት ደግሞ የሀገሪታን የኢኮኖሚ ስርአት እና የተለያዩ ክፍለ ኢኮኖሚዎችን የሚያስተሳስር የሀገሪቱአን ተጨባጭ ሁናቴ ከመልከአምድር፣ከሰው ሀይል አንፃር ያገናዘበ የጠራ እና ከፖለቲካ ፍጆታ በዘለለ መልኩ ተግባራዊ የሚሆን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ያስፈልጋል ይህ ፖሊሲ ደግሞ የሚነደፈው በፖለቲካ ርእዮተ አለም መነፅር ብቻ በሚያስቡ እና በአድርባይ ባለሙያዎች ሳይሆን ከዛ በዘለለ ከሀገር ፋይዳ አኩአያ በሚያስቡ ባለሙያዎች እና ጉዳዩ በሚመለከታቸው ነፃ ቋአማት ነው ይህን ማድረግ ሲቻል ከላይ የጠቀስኩትን የልማታዊ መንግስትን አላማ ማሳካት ይቻላል የኢሃዴግ መንግስት ልማታዊ መንግስት እንደመሆኑ ከላይ ከጠቀስኩት የልማታዊ መንግስት አላማ ጋር ተቃርኖ ውስጥ የሚከተው ለጥቅም ሲሉ የተሰገሰጉት አባሎቹ ልማታዊ መንግስትን ከመተግበር አኩአያ ብቃታቸአው ጥያቄ ምልክት ውስጥ ስለሚገባ ነው ለዚህም ማስረጃ የሚሆነን ስንተኛው እንደሁነ በማላስታውሰው በሃዋሳ በተካሄደው የኢሃዴግ መደበኛ ጉባኤው የቀድሞው የኢሃዴግ ሊቀመንበር እና የሀገራችን ጠቅላይ ሚኒስተር የነበሩት መለስ ዜናዊ ከአሁን በሁአላ ፍርፋሪ ለመልቀም ሳይሆን የኢሃዴግ አባል የሚኮነው የኢሃዲግን ፖሊሲ ለማስፈፀም እንጂ ብለው ሲናገሩ የልማታዊ መንግስትን ንድፈ ሀሳብ ለመተግበር ብቁ ባለሙያዎችእንደሚያስፈልግ በመገንዘባቸው እና በአባሎቻቸው የልማታዊ መንግስትን ፖሊሲ የማስተግበር ብቃት ላይ ባለመተማመን ይመስለኛል ፡፡ በልማታዊ መንግስት ንድፈ ሀሳብ መነሻ ልማታዊ መንግስታት ህዝቦቻቸውን ለልማት የሚያነሳሱበት (በጃፓን እና የሆላንድ የልማታዊ መንግስታት የሀገራቸውን የቀድሞ ታሪክ ለህዝቦቻቸው ማነቃቂያነት እንደተጠቀሙበት ሁሉ) የሀገራቸውን ታሪክ መነሻ በማድረግ የህዝቦቻቸውን ታሪካዊ የሆነ ማህበራዊ፣ ህብረብሄራዊ ወዳጅነት እና ኢኮኖሚያዊ ስልጣኔ በማጉላት ለኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻቸው ትግበራ መነቃቂያነት እና ከማህበረሰቡ ጋር ውል ማሰሪያነት ማዋላቸው ሲሆን የኢሃዴግ መንግስት እንደ ልማታዊ መንግስት በሀገራችን የታሪክ ዘመን ላይ እንኩአን ባለው ምልከታ (የኢትዮጲያ ታሪክ
የ 100 አመት ነው የሚለውን ንግግር ልብ ይሉአል) ከልማታዊ መንግስት ንድፈ ሀሳብ ጋር ተቃርኖ ውስጥ ይከተዋል፡፡

በአብዛኛው ስለ ልማታዊ መንግሰት ሲወሳ አብሮ የሚነሳው መንግስታት ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በሁአላ በጃፓን እና በምስራቅ ኤሽያ ኢንደስትሪን ከማስፋፋት አኩአያ የተጫወቱት ሚና ነው፡፡ በጊዜው መንግስታት ከታሪፍ ከለላ እስከ ድጎማ እና ሌሎች ለኢኮኖሚው ይበጃል የሚሉትን የቁጥጥር ፖሊሲዎችን ለኢኮኖሚው ወሳኝ በሆኑ ክፈለ ኢኮኖሚዎች ላይ ሲከተሉ ነበር፡፡ በልማታዊ መንግስት ንድፈ ሀሳብ መንግስት ኢኮኖሚውን ይቆጣጠራል ሲባል በቁጥጥር ስርአቱ በሀገር ውስጥ በግብርናው እና በኢንደስትሪዎች መሃል ተስስር በመፍጠር የሀገር ውስጥ አምራቾችን እና አርሶአደሮችን አቻ ካልሆነ የውጪ ፉክክር ያድናል ማለት ሲሆን በተጨማሪም በሃገር ውስጥ አምራቾች ሊሟላ ያልቻለውን አቅርቦት በውጪ ባላሀብቶች እና ካምፓኒዎች በሟሟ ላት ቀስ በቀስ በሀገር ውስጥ የሚመረትበትን ሁኔታ የሚያመቻች ሁኔታ የሚፈጥር የቁጥጥር ስርአት ይዘረጋል ማለት እንጂ የሽንኩርት እና የበርበሬ ዋጋ ተመን ያወጣል፣ለምርጫ ቅስቀሳ ገንዘብ ያላዋጡትን የኢኮኖሚው አውታር የሆኑትን ባለሃብቶች ከኢኮኖሚ ስርአቱ ያስወግዳል ማለት አይደለም፡፡

እንደ መውጫ

አሁን በለንበት ዘመን የቴክኖሎጂ መስፋፋት በተለያየ አጥናፍ የሚገኙትን የአለማችንን ሕዝቦች ያለ መንግስታት የዲፕሎማሲም ሆነ የኢኮኖሚ ግንኙነት እርስ በእርስ እንደግለሰብ የሚነጋገሩበት እና የሀጋራቸውን ልምዶች በግለሰብ ደረጃ የሚለዋወጡበትን እድል የፈጠረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ህብተረተሰቡን በአይዶሎጂ እና የእከሌ ሀገር እዚህ የደረሰው በዚህኛው መንገድ ነው የሚል የአይዶሎጂ ማወናበጃ ጊዜ እንዲያልፍበት ምክንያት ሆኑአል፡፡ ጊዜው የህዝቦችን ድህነት ከመቅረፍ አኩአያ የዜጎች ዲሞክራሲ በሸማቾች ዲሞክራሲ መነፅር የሚታይበት ሲሆን የሸማቾች ዲሞክራሲ ደግሞ የመንግስትን የማስተዳደር ሚና ልክ እንደ ሱቅ ውስጥ እነደሚሸጥ እቃ ሸማቹ ከተመቸው ይገዛዋል ካልተመቸው አይገዛውም ከሚለው የግብይይት መርህ ጋር የተመሳሰለ ሲሆን ይህ ማለት ደግሞ መንግስታት በዜጎቻቸው ላይ ተጨባጭ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ካመጡ ይገዛሉ (ይመረጣሉ) ካላመጡ ደግሞ የሚገዛቸው (የሚመርጣቸው) የለም የማይገዛ እቃ ደግሞ ጊዜው ያልፍበታል፡፡ እንደ እኔ እምነት የሀገራችን መንግስት የልማት አጀንዳው የፖሊሲ መነሻ ህዝቡን ተሳታፊ ብቻ የሚደርግ ሳይሆን ተጠቃሚም በሚያደርግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እና ስርአት ላይ የተገነባ ሊሆን ይገባል ይህን ለማድረግ ደግሞ ከጊዜው የሀገራችን የድህነት ስፋት አኩአያ የዲሞክራቲክ ልማታዊ መንግስት መርህ (ዲሞክራሲን እና የኢኮኖሚ እድገትን በአንድ ላይ) አማራጭ የሌለው ይመስለኛል፡፡

Advertisements

One response

  1. best idea

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: