የመንግስት ሚና በካፒታሊስት ኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ ውስጥ!

ስለ ካፒታሊዝም የህይወት ታሪክ ለማተት በጣም አስቸጋሪና ውስብስብም ነው። ይሁንና በካፒታሊስት የገበያ ኢኮኖሚ ታሪክ ውስጥ መንግስታት የተጫወቱትን ሚና መረዳቱ እጅግ አስፈላጊ ነው። ማለት ይችላል ከ14ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ፣ ህብረ-ብሄሮች ከመቋቋማቸው በፊት የነበሩ ትናንሽ መንግስታት በየክልላቸው የመንግስት ኢኮኖሚ ወይም ካሜራሊዝም እየተባለ በሚታወቀው ኢኮኖሚያቸው እንዲያድግ አስፈላጊውን ሚና ተጫውተዋል። በተለይም በኢጣሊያን፣ በአውስትሪያና በጀርመን ትናንሽ መንግስታት ዘንድ ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ ኢኮኖሚዎችን በማደራጀት፣ የዕደ-ጥበብ ስራዎችንና የንግድን እንቅስቃሴ በመደገፍ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ይህንን የተመለከቱት እንደ እነ አንግሊዝ የመሳሰሉት በ16ኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ላይ ከጣሊያን በመኮረጅ ከጥሬ-ሀብት አምራችነትና ወደ ውጭ ላኪነት በመላቀቅ በመንግስት የተደገፈ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንድታካሄድ ተገዳለች። በዚህም መሰረትና አውሮፓ ውስጥ በተፈጠረው የሃይማኖት ውዝግብ ተጠቃሚ ሆና የወጣችው እንግሊዝ በካቶሊክ ሃይማኖት አክራሪነት ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የተባረሩትን የዕደ-ጥበብና የንግድ አዋቂዎቻ ምሁራን በማሰባሰብና ድጋፍ በመስጠት ለኢንዱስትሪ አብዮት የሚሆናትን ሁኔታዎች በአጋጣሚዎች ታዘጋጃለች። በዚህ መልክ ወደ ውስጥ በካፒታሊዝም የሚንቀሳቀስ ኢኮኖሚ በመገንባት ወደ ውጭም የበላይነትን እየተቀዳጀች ትመጣላች። የውጭ ንግድንም ምንነት በመረዳት ደካማ አገሮች እንዲቀበሉት ትሰብካለች።

በኋላ የመጡ እንደፈረንሳይና እንደ ጀርመን የመሳሰሉ አገሮች፣ ፈረንሳይ በ18ኛው ክፍለ-ዘመን፣ ጀርመን ደግሞ በ19ኛው ክፍል-ዘመን አግሬሲቭ የሆነ በመንግስት የተደገፈ፣ ግን ደግሞ በማኑፋክቱር ላይ የተመረኮዘ የውስጥ ገበያ መስፋፋት ስትራቴጂ ይከተላሉ። ይህንን ለማድረግ ንቁ የተባሉ ኃይሎችን በተለያዩ መሳሪያዎች በመደገፍ የካፒሊዝምን ዕድገት ያፋጥናሉ። አገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን ኢንዱስትሪዎች ከውጭ በሚመጣ ተመሳሳይ ዕቃ እንዳይዳከሙ የታሪፍ ዕገዳ ፖሊሲ ይከተላሉ። በተጨማሪም ከተማዎችን በመቆርቆርና እንዲስፋፋ በማድረግ፣ ድልድዮችንና ካናሎች እንዲሰሩ፣ ትምህርት ቤቶች እንዲቋቋሙ በማድረግና ህብረተሰቡ እንዲተሳሰር ልዩ ልዩ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ለካፒታሊዝም ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርገዋል። እንደ ጀርመን የመሳሰሉት አገሮች ደግሞ በከፍተኛ ዕውቀት የተካኑ ምሁራን በመንግስት መኪና ውስጥ በመግባት ኮንሰርቫቲብ ኃይሎችን በመጋፋትና፣ ወደ ውጭ ደግሞ ከተገለጸላቸው ምሁራን ጋር በማበር ጥበባዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ተግባራዊ እንዲሆን ይታገላሉ።

በ19ኛው ክፍል-ዘመን በተለይም እንግሊዝን እየተዘዋወሩ የጎበኙ የጀርመን ልዑካን በእንግሊዙ አሰቃቂ የካፒታሊዝም ዕድገት በማዘን ወደ አገራቸው ሲመለሱ ጥበባዊ ለሆነ የኢኮኖሚ ዕድገትና ለተሰበጣጠረ የኢንዱስትሪ መስፋፋት ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። በተለይም ከግሪኩ ስልጣኔ ጋር በመተዋወቅ ጄናራሎችና ዝቀተኛ ኦፊሰሮች ሳይቀሩ ጀርመን ምን ዐይነት የኢኮኖሚ ዕድገት መከተል እንዳለባት፣ የመንግስትም ሚና ምን መሆን እንዳለበት፣ ከተማዎችና መንደሮች አንዴት መገንባትና መደራጀት እንዳለባቸው፣ ምን ምን ዐይነት የትምህርት ዝግጅቶች ለስልጣኔው እንደሚያበጁ ይመካከራሉ። ይህንንም በስራ ላይ ለማዋል ይታገላሉ። በንጉሱ ላይ ተፆኖ በማድረግ ለጀርመን አንድ መሆን አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ፣ ወደ ውስጥ በተለያዩ የጀርመን ትናንሽ መንግስታት መሀከል የግምሩክ አንድነት ስምምነት በማድረግ የውስጥ ገበያ እንዲያድግ ይደረጋል። በዚህ ዐይነቱ ግፊትና ዕውቀት፣ ከውጭ ደግሞ በምሁራን በመደገፍና በመከራከር የጀርመን የኢኮኖሚ ዕድገት የተቃናና፣ ሁለት ትውልድ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ጀርመን እንግሊዝን ቀድማ ትሄዳለች። ይህ ዐይነቱ እንቅስቃሴ በዓለም ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ዐይነት ለፈላስፎች፣ ለገጣሚዎች ለደራሲዎችና ለፈጣሪዎች በሩን ይከፍታል። ከዚህ የምንማረው ምንድነው? በፈረንሳይና በጀርመን ብቻ ሳይሆን፣ በጃፓን፣ በአሜሪካና በደቡብ ኮርያ የየመንግስታት ሚና፣ እንደየሁኔታው በየአገሩም ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ፣ የውስጥ ገበያ እንዲያድግና ህዝብ እንዲተሳሰር አስፈላጊውን እርምጃ ወስደዋል።

ከዚህ ስንነሳ ይኸኛውን ወይም ያኛውን የኢኮኖሚ ፖሊሲና ቲዎሪ የመከተሉ ጉዳይ አይደለም ዋናው ቁም ነገር። ለአንድ አገር ዕድገት ድርጅትና ፍላጎት ቅድሚያውን ቦታ ይይዛሉ። ከዚህ ጋር ተደምሮ ፕሪንስፕል ያስፈልጋል። ከዚህ ስንነሳ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ እንደጀርመንና ፈረንሳይ የመሳሰሉት በጦርነት የተመታውን ኢኮኖሚያቸውን በ15 ዐመታት ውስጥ መልሰው መገንባት የቻሉት በተቀነባበረ የመንግስት ድጋፍና ህዝባዊ ተሳትፎ ነው። ከፍተኛ ፍላጎትና ቆራጥነት ስለነበራቸው ነው። በተንኮል ስራ በመጠመድ አልነበረም እዚህ የደረሱት። እንደዚህ ዐይነቱ ቆራጥነት የበሰለ ፖለቲካና ባህልን የሚጠይቅ ነው። ሁለቱም አገሮች እንደሚባለው በተራ የነፃ ገበያ አማካይነት ኢኮኖሚያቸውን አልገነቡም።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: