የኢኮኖሚ ዕድገትና የኢኮኖሚ ስርዓት ጥያቄ!

ከስድሳ ወይም ከዚያ ዐመታት በላይ የዓለምን ህዝብ ያወናበደውና ግራ ያጋባው ምንም ሳይንሳዊ መሰረት መሰረት ሳይኖረው ዝም ብሎ የገበያ ኢኮኖሚ እየተባለ በጥቅሉ የሚነፍሰው አባባል ነው። የሰው ልጅ በአንድ ቦታ ረጋ ብሎ መቀመጥ ከጀመረና በስራ ክፍፍል መደራጀት ከጀመረ ወዲህ የገበያ ልውውጥ አስፈላጊ እየሆነ ሊመጣ ችሏል። እንደሚታወቀው ማንኛውም አምራች ግለሰብ የሚፈለገውን ነገር ሁሉ ራሱ ማምረት ስለማይችል፣ ሌላው ያመረተውን ገዝቶ ለመጠቀም ሲል ዕቃውን ገበያ ላይ አውጥቶ ይሸጣል፤ ይገበያያል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ቀሰ በቀስ እያለ ለገንዘብ መፈጠርና በተለያየ መልክ መገለጽ በር እየከፈተ መጣ። በዚህ መልክ የገበያ ኢኮኖሚ መፈጠር፣ ማደግና መስፋፋት ጀመረ። ይህ ሀተታ ግን ሙሉ በሙሉ ሳይንሳዊ አይደለም። ሳይንሳዊ ሊሆን የሚችለው ኢኮኖሚው የሚንቀሳቀስበት ስርዓት ግልጽ ሆኖ ሲተነተን ነው። ይህ እስካልሆነ ድረስ በውዥንብር ዓለም ውስጥ እንኖራለን ማለት ነው። ይህም በራሱ ደግሞ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚለውንም ትርጉም በደንብ እንዳንረዳ ሊያደርገን ይችላል።

ይህ ችግር የመነጨውና የሚመነጨው በየትምህርት ቤቱና በየዩኒቨርስቲው የሚሰጠው የኢኮኖሚ ትምህርት፣ ሚክሮና ማክሮ ኢኮኖሚ፣ በጊዜ ያልተገደበ፣ ልክ እንደ እግዚአብሄር፣ የሰው ልጅ፣ ተፈጥሮና ህዋ ከመፈጠራቸው በፊት እንደነበረና እንዳለ፣ ወደፊትም እንደሚኖር ተደርጎ በብዙዎቻችን ዘንድ እንደ አመኔታ ሰለተወሰደና ስለሚወሰድ ነው። በዚህ መልክ የቀረበው የኢኮኖሚ ትምህርት ታሪካዊ ሳላይደለ ስለስርዓት ሊያወራልን አይችልም። ስለሆነም በማንኛውም አገር፣ ብዙ ነገሮችን፣ ለምሳሌ ስለባህልና የዕድገት ደረጃ፣ ስለታሪካዊ አመጣጥ፣ ስለ ጠቅላላው የኢኮኖሚ አቀነጃጀት ሁኔታና ከላይ የዘረዘርኳቸውን የቦታና የጊዜ ጥያቄ ከቁጥር ውስጥ ሳያስገባ የገበያ ኢኮኖሚ የሚለው ጽንሰ-ሃሳብና ፖሊሲው በሁሉም አገር ተግባራዊ ሊሆን ይችላል፤ ይህም የተፈጥሮ ህግ ነው ይለናል። በዚህ መልክ ታሪክንና ባህልን፣ እንዲሁም የህሊናን አወቃቀርና የምርት ኃይሎችን(Production factors and Production forces) የዕድገት ደረጃ ስሌትና ትንተና ውስጥ ያላስገባ ፖሊሲ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ ከተወሳሰበ የገበያ ኢኮኖሚ ጋር ያላደጉ ህብረተሰቦችንና ፖሊሲ አውጭዎችን መቀመቅ ውስጥ ነው የሚከታቸው። የተወሳሰበና በቀላሉ ሊፈታ የማይችል የህብረተሰብ ችግር ነው የሚፈጠረው። የሰው ልጅ አቅጣጫውንና የኑሮ መመሪያ የሚሆነውን ነገር ነው እንዳያገኝ የሚደረገው። በዚህም ምክንያት ቢያንስ ባለፉት ሰላሳ ዐመታት ውስጥ በገበያ ኢኮኖሚና በግሎባላይዜሽን ስም የተካሄዱት ጣልቃ-ገብነቶችና ወረራዎች በየአገሮች ውስጥ ዱርዬነትንና የማፊያ ተግባርን፣ የሴተኛ አዳሪዎች ብዛትና፣ ከተፈጥሮ ህግ ጋር የማይሄዱ የፍትወ-ስጋ ድርጊቶችን፣ የሀብት ክፍፍል መዛባትን፣ ባጭሩ ድህነትን ማሳፋፋት የዚህ ዐይነቱ በተሳሳተ መልክ የሚቀርብ የገበያ ኢኮኖሚ አነጋጋርና ትምህርት ነው። በመሆኑም አንድን አገር እንደ አገርና እንደ ህብረተሰብ እንዳይገነባ በማድረግ ሁሉም ነገር ካለስርዓትና ልቅ በሆነ መልክ በመካሄድ ጉልበተኛው ባሸናፊነት የሚወጣበት፣ ደካማው ደግሞ የሚረገጥበትና እንደቆሻሻ የሚጣልበት ሁኔታን እንመለከታለን።

ያም ሆነ ይህ ስለ ኢኮኖሚ ስርዓት በምናወራበት ጊዜ ስለ ምርት ኃይሎች፣ ስለ ምርት ግኑኝነትና፣ እነዚህ ደግሞ በምን ዐይነት ስርዓት ውስጥ እንደሚካሄዱ ማወቅ አለብን። ይህንን ስንገነዘብ ብቻ ነው ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት ማውራት የምንችለው።እንደሚታወቀው ቢያንስ ከሰላሳ ዐመታት ጀምሮ የዓለም ኢኮኖሚዎች መለኪያ ሁሉ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ስርዓት ሆኗል። ስለሆነም ይህንን መረዳት ያስፈልጋል።

አንድ ሳናውቀው በጭንቅላት ውስጥ የቋጠርነውና እንደልማድ የወሰድነው ነገር አለ። ይኸውም ዛሬ በምዕራብ አውሮፓ ያለው ስርዓት፣ 1ኛ) የገበያ ኢኮኖሚ ነው የሚል፣ 2ኛ) ይህ ስርዓት በሂደት መልክ ከብዙ መቶ ዐመታት መነሳትና መውደቅ በኋላ እዚህ ደረጃ የደረሰ ሳይሆን፣ ትላንት የነበረ፣ ዛሬም ያለና ነገም የሚኖር፣ 3ኛ) ይህም የገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት ሁሉም በእኩል ደረጃ የሚሳተፉበትና፣ ለሁሉም ክፍት የሆነና፣ ሁሉም ሊበለጽግበት የሚችል ስርዓት ተደርጎ ነው በሁላችን ዘንድ ግንዛቤ ውስጥ ያለው። ስለሆነም ካፒታሊዝም በምርት ግኑኝነትና በምርት ኃይሎች የሚገለጽ ሳይሆን፣ በተራ አነጋገር በገበያ ኢኮኖሚ ብቻ የሚገለጽ ነው። ይህ ዐይነቱ አባባል በእኛ የተለመደውን ያህል፣ በካፒታሊስት አገሮች ግን በካፒታሊስቶችና የመንግስትን መኪና በጨበጡ እንዲያው በደፈና የገበያ ኢኮኖሚ እየተባለ የሚገለጽ ሳይሆን፣ ማህበራዊ የገበያ ኢኮኖሚ ወይም የካፒታሊስት የገበያ ኢኮኖሚ እየተባለ ነው። አሁንም ድርቅ ብለው አይን ባወጣ መልክ ሰውን ለማሳመን በሚፈልጉት የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች አመለካከት፣ የገበያ ኢኮኖሚ በእነ አዳም ስሚዙ ዘመን እንደሚታየው በትናንሽ ከበርቴዎችና ውድድር በሰፈነበት ዘመን ዐይነት የሚካሂድ ንፁህ ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ ካልሆነ በስተቀር፣ የዛሬው የገበያ ኢኮኖሚ በጣም የተወሳሰበና ፕሮፌሰር ሶዲ እንደሚሉት ግራ የሚያጋባ ነው። በዚህም መሰረት በኢኮኖሚ ክንዋኔ ውስጥ የሚሳተፍ በሙሉ እንደ አስተዋፅዖው ከፍተኛ ትርፍና ከፍተኛ ጥቅም የሚያገኝ አይደለም። በመሆኑም በተጨባጭ ዓለም ውስጥ በሚካሄደው በኢኮኖሚው ዓለምና በፎርማል ደረጃ በተጻፈው ነገር ከፍተኛ ልዩነት እንዳለ መመልከት ይቻላል።

እንደሚታወቀው የዛሬው የካፒታሊስት ስርዓት ከሶስት መቶና አራት መቶ ዐመት በፊት የነበረው ዐይነት አይደለም። የዐይነት ለውጥ የሚታይበትና፣ በአብዛኛው ጥቂት አምራቾችኛ አቅራቢዎች(Oligolopolists) ገበያውን የሚቆጣጠሩበትና፣ የሀብት ክምችትም በጥቂት ሰዎች እጅ የሚገኝ ነው። ይህ የስርዓቱ መግለጫ ሲሆን፣ በመሰረቱ ካፒታሊዝም በውድድር አማካይነት የሚንቀሳቀስ ውስጠ-ኃይሉ ከፍተኛ የሆነና፣ በተወሰነ ክልል ብቻ ሊገደብ የሚችል አይደለም። በገበያ ላይ የሚሳተፉ አማራቾችም ሆነ ነጋዴዎች በማያቋርጥ ውድድር ውስጥ የሚገኙና፣ ከገበያ ላለመውጣት ሲሉ ወይም ደግሞ ባሸናፊነት ለመውጣት በየጊዜው የፈጠራ ክንውንና(Innovation) የቴክኖሎጂ ለውጥ ማድረግ አለባቸው። በዚህ ዐይነቱ የማያቋርጥ ውድድር የማምረቻ ዋጋን በመቀነስ ለተጠቃሚው ደግሞ በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባሉ። ይህንን ለማድረግ ሲሉ ደግሞ የግዴታ አዳዲስ ማሽኖች መግዛትና መትከል ሳለለባቸው ከባንኮች ጋር በመቆላለፍ በባንክ ብድር ጥገኛ ይሆናሉ። ይህ ዐይነቱ ከታች ወደ ላይና ወደ ጎን የተቆላለፈ ስርዓትና የምርት ክንውን ለገበያ መስፋፋት የግዴታ ግፊትን ያደርጋል። ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በገበያው ውስጥ ገብቶ ሳያውቀው ተዋናኝ ይሆናል። በኬይንስም አገላለጽ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ በገንዘብ ኃይል በሁሉም ረድፍ የተሳሰረና፣ ገንዘብ ዛሬንና ነገን የሚያገናኝ ሆኖ በመውጣት ኢኮኖሚያዊ ሂደትን ይወስናል። እንደዚህ ዐይነቱ ኢኮኖሚያዊ ስርዓት ልዩ ስለሆነና የራሱ ህግ ስላለው፣ ቀውሱም ልዩ ዐይነት ቀውስ ነው። በሌላ አነጋገር አሁንም በኬይንስ አነጋገር የካፒታሊስት ኢኮኖሚ እንደየሁኔታው ከፍና ዝቅ የሚል ወይም ደግሞ በልዩ ቀውስ የሚገለጽ ነው። የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ቀውስ በመሰረቱ የስትራክቸራል ቀውስ ሳይሆን በየጊዜው ከፍና ዝቅ(Conjectural Crisis) የሚገለጽ ሲሆን፣ ከእንደዚህ ዐይነት ቀውስ ውስጥ የሚወጣው ሹምፐተር እንደሚለው በራሱ አጥፊነትና አልሚነት(Creative Destruction) ኃይል ነው። ይህ ማለት ያረጁ ቴክኖሎጂዎች ቦታ ሳይኖራቸው ሲቀር በውድድር ዓለም ውስጥ የሚከንፈው ካፒታሊስት የግዴታ ያረጀውን ማሽን በአዳዲሶች ይተካል። ያረጁት ማሽኖች እንደየሁኔታው አይ ይጣላሉ፣ አይ ለሌላ አገር ይሸጣሉ፣ ካሊያም ደግሞ ሪሳይክልድ በመሆን እንደ ጥሬ-ሀብት ያገለግላሉ። ይህም ማለት የካፒታሊስት ኢኮኖሚ በማያቋርጥ ፈጠራ(Innovation) የሚገኝ ልዩ ዐይነት ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ ነው። ይህ ማለት ግን ገደብ የለውም ወይም ስርዓቱ ዘለዓለማዊ ነው ማለት አይደለም።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: